የግብጽ ፓርላማ የሰብዓዊ መብት ንኡስ ኮሚቴ  የሳኡዲ አረቢያ ባለስልጣናት ሰሞኑን በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ዙሪያ ተወያየ።

ታኅሣሥ ፲፪ (አሥራ  ሁለት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ዘ- ኢጂፕሺያን ኢንዲፐንደንት እንደዘገበው  ውይይቱ ያተኮረው በሳኡዲና በግብጽ መካከል ቅሬታ በተፈጠረበት በአሁኑ ሰዓት የሳኡዲ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ  ያደረጉት ጉብኝት- በአባይ ላይ እየተሰራ ካለው ግድብ ጋር  ስለመያያዙ ነው።

የሳኡዲ ንጉስ አማካሪ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ባደረጉት ጉብኝት ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ  ባለስልጣናት ጋር መገናኘታቸው ታውቋል።

ይህ የሳኡዲ ባለስልጣናት ጉብኝት ከአባይ ግድብ ጋር ግንኙነት  ይኖረው ይሆን ወይ በማለት  በፓርላማው ሀሳብ  መሰንዘሩን ተከትሎ የግብጽ የምክር ቤት ባል ማጂዲ ሰይፍ  ጉብኝቱ ከግድቡ ጋር ግንኙነት ይኑረው ወይም አይኑረው አለመረጋገጡን ተናግረዋል። ሰይፍ አክለውም “የግብጽ የፖለቲካ አመራር በራስ መተማመን ሊኖረው ይገባል” ብለዋል።

“ሳኡዲ አረቢያ ትክክለኛውን ነገር ልትቀበል ይገባል” ያሉት  የፓርላማ አባል ሰኢድ ሻባቤክ በበኩላቸው፤ የቲራንና ሳናፊር ደሴቶች የግብጽ ግዛቶች ናቸው ብለዋል። ላለፉት አስርት ዓመታት ሳኡዲ ስታስተዳድራቸው በቆዩት ሁለቱ ደሴቶች መካከል በግብጽና በሳኡዲ መካከል ውዝግብ ከተፈጠረ ሰንበት ብሏል።

የሳኡዲ ባለስልጣናት ትናንት ማክሰኞ  ከግብጽ ወደ ሳኡዲ በሚገቡ ሁሉም አይነት የቃሪያ ምርቶች ላይ እገዳ ጥለዋል። ሀገራቱ በቲናርና ሳናፊር ደሴቶች ዙሪያ የጀመሩት አታካራ ወዴት ያመራ ይሆን የሚለው የአካባቢው ሀገራት መነጋገሪያ ሆኗል።