(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 15/2011) የግብጽ ወታደራዊ ልዑካን በመጪው ጥቅምት ወር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚወጡ ተገለጸ።
የግብጽ ወታደራዊ ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉዞ ምንን መሰረት ያደረገ እንደሆነ የተገለጸ ነገር ባይኖርም በጥቅምት ወር መጀመሪያ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ተመልክቷል።
በግብጽ ኢንተርናሽናል ኢኮኖሚ ፎረም ዳይሬክተር የሆኑት ግብጻዊው አደል አልአዳዊ በቲውተር ገጻቸው ዕሁድ ዕለት ባሰራጩት መረጃ ውይይቱ ጠቃሚ እንደሚሆንም አመልክቷል። ግብጻውያኑ ወታደራዊ ልዑካን በቁጥር ምን ያህል እንደሚሆኑና በማን እንደሚሰሩ የተገለጸ ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የሕዳሴውን ግድብ የውሃ አሞላል በተመለከተ የኢትዮጵያ፣ የግብጽና ሱዳን ሚኒስትሮች ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ ተቀምጠዋል።
ከሶስቱ ሃገራት የተውጣጡ 15 አባላት ያለበት ቡድን ያጠናውን ሳይንሳዊ ጥናት መነሻ በማድረግ ስለውሃ አሞላሉ ለመነጋገር አዲስ አበባ የተቀመጡት የሶስቱ ሃገራት ሚኒስትሮች እስከ ነገ ስብሰባቸውን ይቀጥላሉ ተብሉ ይጠበቃል።
10.2 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የሚይዘውን የሕዳሴ ግድብ ለመሙላት 15 ዓመታት ያህል መውሰድ እንደሚገባው በግብጽ በኩል ሃሳብ የቀረበ ሲሆን ኢትዮጵያ ከዚያ በግማሽ ባነሰ ግዜ ውስጥ መሙላይ ይኖርባታል የሚል አቋም ይዛለች።
የህዳሴው ግድብ በተገባው ቃል መሰረት ቢሆን ኖሮ በዚህ ዓመት ስራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምር ነበር።