የግብጽ ምሁራን ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር በምታደርገው ድርድር ጊዜዋን እያጠፋች ነው አሉ

ኢሳት (ሃምሌ 13 ፥ 2008)

የታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ በኢትዮጵያና በግብፅ መካክል እየተደረገ ያለው ድርድር ወደተሳሳተ አቅጣጫ እየሄደ ሲሉ የግብጽ የውሃ ሃብት ምሁራን ስጋታቸውን ገለጹ።

በካይሮ ዩኒቨርስቲ የውሃን ሃብት ፕሮፈሰር የሆኑት ናደር ኖር ኤልዲን /ዴይሊ ኒውስ ለተባለ ጋዜጣ ሲናገሩ፣ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የተስማሙበት የአማካሪዎች ጥናት ለግብጽ የሚሰጠው ምንም ጥቅም የለም በማለት ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር በምታደርገው ድርድር ጊዜዋን እያጠፋች እንደሆነ መናገራቸው ተገልጿል።

ምሁሩ ሲናገሩ የአባይን ግድብ የተመለከቱ ጥናቶቹ 17 ወራት ይወስዳሉ ቢባልም ኢትዮጵያ ምን አልባትም በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ አብዛኛውን የግድቡን ክፍል ልታጠናቅቅ ትችላለች” በማለት የግብጽን መንግስት ቸልተኝነት መውቀሳቸን ዴይሊ ኒውስ ዘግቧል።

ሌሎች የግብፅ ምሁራን በበኩላቸው ጥናቱ የግድብ ግንባታውን ስለማያስቆም፣ አሁን በግብፅ በሱዳንና በኢትዮጵያ ስምምነት እየተደረገ ያለው ጥናት ለግብጽ የሚፈይደው ነገር የለም ሲሉ ተናግረዋል። ከ17 ወራት በኋላ የሚጠናቀቀው ይኸው ጥናት ግድቡ ከተጠናቀቀ በኋላ ስለሚደርስ በግድቡ ላይ ተፅዕኖ አይኖረውም ሲሉ ተከራክረዋል።

ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች ግድቡ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ለማጥናት እንቅስቃሴ  ላይ ሲሆኑ፣ የግብጽ መንግስት ግን የጥናቱ ውጤት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ትገልጻለች።

ናደር ኖር ኤልዲን በበኩላቸው ግብጽ ጉዳዩን በአጭር ጊዜ ወደ አለም አቀፍ ፍርድ ቤት መውሰድ እንደሚኖርባትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የግድቡ ግንባታ የሚያመጣውን ተጽዕኖ መመርመር ይኖርበታል ማለታቸውን ተከትሎ “አደጋው አለ፣ ያንን አደጋ ግብጽ የምትከላከልበት ህጋዊ አግባብ አሁን ነው ሲሉ የካይሮው  የውሃ ሃብት ፕሮፌሰር ለጋዜጣው ተናግረዋል።

በተጨማሪም “ግብፅ በምታገኘው የውሃ ይዞታዋ ላይ መደራደር ይኖርባታል፣ አለበለዚያ መብቷን አሳልፋ እየሰጠች ነው” ሲሉ ለግብጽ መንግስት ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

የግብጽ ባለስልጣናትና ምሁራን የአባይን ግድብ በማስመልከት በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና፣ ግብጽ የሚደረገው ውይይት እንዳላስደሰታቸው ሲናገሩ ቆይተዋል። በቅርቡ በግብፅ ፓርላማ የመከላከያና የደህንነት ጉዳዮች ኮሚቴና የፓርላማ አባል ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር በአባይ ግድብ ዙሪያ ያላትን ልዩነት በወታደራዊ እርምጃ ብቻ የሚፈታ ነው ሲሉ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው “ጥቃትን እንደአማራጭ” የሚለው ሃሳብ ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን፣ ለንግግር እንኳን የማይቀርብ ነው ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ የጥናቱ ውጤት ምንም ይሁን ምን የግድብ ግንባታውን እንደማታቆም አስታወቀች። የኢትዮጵያ የመስኖና ውሃ ሃብት ሚኒስትር ሞቱማ ሚካሳ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚደረገው የሶስትዮሽ ስምምነት ወይም የጥናቱ ውጤት ግንባታውን እንደማያቆመው መናገራቸው ተሰምቷል። ኢትዮጵያ በሌሎች ወንዞች ላይ ጭምር በርካታ ግድቦችን ለመገንባት ማቀዷን አል ኢጂይፕት ኢንዲፔንደንት ዘግቧል።

ኢትዮጵያና ግብፅ ሱዳንን በማካተት ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ለመመርመር ጥናት እንዲካሄድ ቢስማሙም ግብጽ ግድቡ የወንዙን ፍሰት ይቀንሳል ስትል ስጋቷን በመግለጽ ላይ ናት።

ሁለቱ አገራት ለአመታት መፍታት ያልቻሉትን ልዩነት ተከትሎ የሁለቱ ሃገር ባለስልጣናት ተቋርጦ የነበረው ድርድር ቀጥሎ ጥናቱ እንዲጀመር ፍላጎት ማሳየታቸው በትላንትናው ዕለት መዘገባችን ይታወሳል።