የጣልያን መንግስት ለፊልድ ማርሻል ግራዚያኒ ያቆመው ሀውልትና የመታሰቢያ ፓርክ በኢጣሊያ ውስጥ ተቃውሞ እንደቀሰቀሰ ቢቢሲ ዘገበ።
የቤኔቶ ሙሶሎኒ የጦር መሪ በመሆን፤ በሊቢያና በኢትዮጵያ በፈጸመው ከፍተኛ ፍጅትና ግድያ የተፈረደበት ግራዚያኒ፤ የ160 ሺህ ዶላር መታሰቢያው የቆመለት፤ ከሮም ወጣ ብላ በምትገኝ መንደር ውስጥ ነው።
የኢጣሊያ ዋንኛው ግራ-ዘመም ፓርቲ፤ ግራዚያኒ በ1930ዎቹ ውስጥ በኢትዮጵያ የፈጸመውን የዘር ማጥፋት በማስታወስ፤ በዚህ ዘመን ለግራዚያኒ ይህ መታሰቢያ መቆሙን አጥብቆ አውግዟል።
ፌዛን በምትባለው የሊቢያ ስፍራ በሱ ትእዛዝ በሞቱት ሊቢያዊያን ምክንያት “የፌዛኑ አራጅ” በመባል የሚታወቀው ግራዚያኒ፤ በኢትዮጵያውያን ላይ የመርዝና ኬሚካል ጋዝ በመጠቀም ብዙ ሺህ ኢትዮጵያዊያንን እንደጨረሰ ይታወቃል።
ግራዚያኒ፤ በ1948 በጦር ወንጀለኝነት ተወንጅሎ የ18 ዓመት እስራት ቢፈረድበትም፤ ከ2 አመታት እስር በሁዋላ ተፈቶ፤ በ1955 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል ሲል ቢቢሲ አትቷል።