ኢሳት (ጥር 15 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ተሰማርተው የሚገኙ የግል ባንኮች በብሄራዊ ባንክ የተቀመጠላቸውን መነሻ ካፒታል ማሟላት ካልቻሉ ውህደት እንዲፈጸሙ እንደሚደረግ የብሄራዊ ባንክ ይፋ አደረገ።
የባንኩ ገዢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የግል ባንኮች ሊኖራቸው በሚገባው መነሻ ካፒታል ላይ አዲስ ጥናት መካሄዱን የገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ባንኮች ካፒታላቸውን ሁለት ቢሊዮን ብር ማድረስ እንዳለባቸው በብሄራዊ ባንክ በኩል መነገሩ ይታወሳል።
ይሁንና፣ በአዲስ ጥናት የግል ባንኮች መድረስ የሚገባቸው የካፒታል መጠን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ይሁን አይሁን አቶ ተክለወልድ ከመግለፅ ተቆጥበዋል።
በጉዳዩ ዙሪይ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ቃለምልልስን ያደረጉት ሃላፊው ባንኮቹን የሚመለከተው መመሪያ በቅርቡ ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምር አስታውቀዋል።
በባንኩ የሚቀመጠውን ካፒታል የሚያሟሉት የግል ባንኮችም እንዲዋሃዱ እንደሚደረግ አቶ ተክለወልድ ለጋዜጣው ተናግረዋል።
መንግስት እንዲህ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት ተጠናክረው እንዲወጡ ሃላፊነት ያለበት ከመሆኑ አንጻር ባንኮች የያዙት ገንዘብ የህዝብ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል ሲሉ የብሄራዊ ባንክ ገዢ አክለው ገልጸዋል። እንደእርሳቸው ገለጻ ባንኮች በአሁኑ ወቅት በቁጠባ የሰበሰቡት ገንዘብ ከ467 ቢልዮን ብር በላይ ይደርሳል።
የመንግስትም ሆነ የግል ባንኮች በድምሩ ያላቸው ካፒታል 30 ቢሊዮን ብር መሆኑን ያመለከቱት ሃላፌው ይህ ካፒታል ገንዘብ ሲቀነስ ቀሪው 437 ቢሊዮን ብር የህዝብ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
ይኸው የህዝብ ገንዘብ በተገቢው መንገድ በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል ብሄራዊ ባንክና መንግስት ማንኛውንም ነገር ያደርጋሉ ሲሉ አቶ ተክለወልድ አስታውቀዋል።
ይሁንና የብሄራዊ ባንክ በግል ባንኮች ላይ ተግባራዊ ሊያደርግ ያሰበው የመነሻ ካፒታል ግዴታ በነባርና አዲስ በሚቋቋሙ ባንኮች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ሊያሳድር እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ላያቸው አካላት ይገልጻሉ።
የመነሻ ካፒታሉ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሆን ከተደረገም ከእንግዲህ በኋላ አዲስ የሚቋቋም የግል ባንክ እንደማይኖርና የባንኮች መስፋፋትን ውድድር ውስን ሊሆን እንደሚችልም እነዚሁ አካላት አስረድተዋል።
መንግስት በተለያዩ ጊዜያት በግል ባንኮች ላይ እያስተላለፈ ያለው መመሪያ በባንኮቹ የስራ እንቅስቃሴ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስታውቀዋል።
ለአመታት በግል ባንኮች ላይ ተጥሎ የቆየውን አስገዳጅ የቦንድ ግዥ መመሪያን ያወሱት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በውጭ ምንዛሪ ዝውውር ላይም 16 የሚሆኑት የግል ባንኮች ጠንካራ ህግ ተግባራዊ ተደርጎባቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የአለም ባንክን ጨምሮ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት በባንኮች ላይ እየተጣሉ ያሉ መመሪያዎች መንግስት የፋይናንስ ዘርፉን ለመቆጣጠር እየወሰደ ያለው ዕርምጃ መሆኑን ሲገልፅ መቆየታቸው ይታወሳል።