መጋቢት 4 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-ኢትዮጵያ የአካባቢ ዉድመት ያስከትላል በተባለዉ አወዛጋቢ የግልገል ጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ሃይል ግንባታ ስራ በአሻፈረኝ ባይነት መግፋቷን አልጀዚራ ገለፀ
በኦሮሚያ ክልል የሚሰራዉ 243 ሜትር ከፍታ የሚኖረዉ የጊቤ 3 ግድብ ከአለም በትልቅነቱ አንደኛ እንደሆነ የሃይልና የዉሀ ሚኒስትር አለማየሁ ተገኑ ለአልጄዚራ ቢገልፁም ግድቡ በተገቢዉ ጥናት ላይ ያልተመሰረተና በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ የሚፈሰዉን የኦሞ ወንዝ መጠን በእጅጉ ሊቀንሰዉ እንደሚችል የአካባቢ ተንከባካቢዎች ይተቻሉ።
በተለይም በታችኛዉ የኦሞ ሸለቆ ሰሜን ኬንያ ቱርካና ሃይቅ አካባቢ በሚኖሩት ሰዎች ህይወት ላይ የሚያሳርፈዉ ተፅእኖ ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል።
የቱርካና ሃይቅ 80 በመቶ ዉሃ ከኦሞ ወንዝ የሚገኝ ሲሆን የግድቡ ስራ ሲጠናቀቅ የሃይቁ የዉሃ መጠን በ1/3ኛ ደረጃ ዝቅ ሊል መቻሉን የገለፁት አንድ የአካባቢ ተንከባካቢ በ5 ወይንም በ10 አመት ዉስጥ በቂ የዉሃ መጠን ስለመኖሩ ጥናት እንዳልተደረገበት አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሰት የወንዙ የፍሳሽ መጠን አይለወጥም ቢልም ብዙዎች አልተቀበሉትም። ይልቁንም የግንባታ ስራዉ እንዲቋረጥ የሚደግፉ ሃይሎች ግድቡ በቋፍ ያለዉን የአካባቢዉን የተፈጥሮ የአየር ንብረት እስከመጨረሻዉ እንደሚያዛባዉና በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያና በሰሜን ኬንያ ነዋሪ የሆኑ ቁጥራቸዉ 500 ሺህ የሚገመቱ ሰዎችን ህይወት በሚያስገርም ደረጃ ጉዳት ዉስጥ ሊጥል እንደሚችል አልጄዚራ ዘግቧል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide