(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 5/2011)በምዕራብ ጉጂ ዞን ቃርጫ ወረዳ ከመንግስት ስራ የተባረሩ የጌዲዮ ተወላጆች የከፋ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ለኢሳት ገለጹ።
ተወላጆቹ እንደሚሉት ከስራ እንዲባረሩ የተደረገው የጌዲዮ ተወላጆች በመሆናቸውና ማንነታችን ይገለጽ፣በቋንቋችን እንማር የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው ነው።
ከስራ ሲባረሩ ያለምንም ክፍያ መሆኑ ደግሞ የነሱንም ሆነ የቤተሰባቸውን ኑሮ አስከፊ እንዲሆን እንዳደረገባቸው ይናገራሉ።
በምዕራብ ጉጂ ዞን ቃርጫ ወረዳ ከሚያዚያ 2010 በፊት የመንግስት ሰራተኛ ነበሩ።
ነገር ግን በጉጂ ዞን በጌዲዮ ተወላጆች ላይ አላግባብ የሆነ ግፍና መፈናቀል ሲፈጸም ከ80 በላይ የሚሆኑ የጌዲዮ ተወላጆች ደግሞ ከመንግስት ስራቸው እንዲባረሩ ተደርጓል።
ሰራተኞቹ ከስራ እንዲባረሩ ምክንያት የሆነውም የጌዲዮ ተወላጅ ከመሆናቸው ሌላ ማንነታችን ይገለጽ፡በቋንቋችን እንማር የሚለውን ጥያቄ በማቅረባቸው መሆኑን ነው ለኢሳት መረጃውን ያደረሱት የጌዲዮ ተወላጆች የሚናገሩት።
ከስራ የተባረሩት ዜጎች በወቅቱ ችግሩ ሲፈጠር ሸሽተን ወደ ደቡብ ክልል ገደብ መግባታቸውንና ነገሮች የተረጋጉ ሲመስሉ ወደ ነበሩበት ቦታ መመለሳቸውንና ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥያቄ ማቅረባቸውን ይናገራሉ።–በወቅቱ የተሰጣቸው ምላሽ ግን እናንተ በዚህ ክልል ስራ መቀጠር የሚችለው የክልሉ ተወላጅ ብቻ ነው የሚል መሆኑን ነው የገለጹት።
ከስራ የተባረሩት የጌዲዮ ተወላጆች እንደሚሉት ከሆነ ከስራ እንዲባረሩ ያደረጓቸው ባለስልጣናትም አሉ።
እንደነሱ አባባል ከሆነ አላግባብ በሆነ መልኩ ከስራ መባረራችንን፡ያለምንም ገቢ ሜዳ ላይ መጣላችንን ሌላው አካል ሰምቶ ምላሽ እንዲሰጠን ብንሞክርም ጆሮ የሚሰጠን አላገኘንም ብለዋል።
እንዲህ አይነቱ ችግር ሲፈጠር የመጀመሪያው ጊዜ አይደለም ይላሉ።በ2008ም የደሞዝ ቅጥራችንንና የሚከፈለንን ደሞዝ የሚገልጽ ደብዳቤ ከደረሰን በኋላ ሙስና ካልከፈላችሁን አንሰጥም በሚል ከተቀጠሩበት ደሞዝ በግማሽ ተቀንሶ እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል።
አሁንም ቢሆን ያለው የሰራተኛ አቀጣጠር ህጉን ያልጠበቀና የትምህርት ደረጃን ማዕከል ያላደረገ፡የሌሎች ብሔሮችን ተዋጽኦ ያገለለ ነው ይላሉ።
እንደ እሳቸው አባባል ከሆነ ለምን እንዲህ አይነት በደሎች ይፈጸማሉ በሚል ጥያቄ ሲያነሱ ከነበሩት መካከልም ሕይወታቸውን ያጡ መኖራቸውን ይናገራሉ።
ከስራ የተባረሩት የጌዲዮ ተወላጆች አሁንም ከነቤተሰቦቻቸው የከፋ ችግር ውስጥ መውደቃቸውንና የሚመለከተውም ለችግራቸው እንዲደርስላቸው ጥሪያቸውን አቅርበዋል።