የጋዜጠኛ ኤፍሬምን ህይወት ለማትረፍ የሚደረገው መዋጮ አርኪ አይደለም ተባለ

ጥቅምት ፳፮(ሃያ ስድስት )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ጥቅምት 20 ቀን 2006 ዓ.ም በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቀረበባቸውን የስም ማጥፋት ክስ ፍ/ቤት ቀርበው ምላሽ

ለመስጠት ወደ ሐዋሳ ያመሩት የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ባልደረቦች ከደረሰባቸው የባጃጅ ተሸከርካሪ አደጋ ጋር በተያያዘ በተለይ ኤፍሬም በየነ ላይ የከፋ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ በመዋጮ ህይወቱን ለማትረፍ እየተደረገ ያለው ጥረት እስካሁን ውጤቱ አመርቂ አለመሆኑን አንድ የዕርዳታ አሰባሳቢ ኮምቴ አባል አስታወቀ፡፡

ጋዜጠኛ ኤፍሬም አደጋው አከርካሪ አጥንቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰ በኃላ ወደ አዲስአበባ የኮርያ ሆስፒታል ተወስዶ ለሁለት ጊዜያት ያህል የቀዶ ጥገና ሕክምና ቢደረግለትም የጤናው ሁኔታ ብዙም መሻሻል አለማሳየቱን
እንዲሁም እስካሁን የታከመበትን 130ሺ ብር እንኩዋን መሸፈን ባለመቻሉ በከፍተኛ ችግር ላይ መሆኑ ታውቆዋል፡፡ ጋዜጠኛው በአሁኑ ሰዓት ሪከቨሪ ተብሎ በሚታወቅ ክፍል ውስጥ ዕርዳታ እየተደረገለት ሲሆን የሙያ አጋሮቹ የሕክምናወጪውን በዕርዳታ ለመሸፈን ኮምቴ አዋቅረው ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ዛሬ

ከሰዓት በኃላ ድረስ በቂ የገንዘብ ድጋፍ አለመገኘቱ ታውቆአል፡፡ በተያያዘ ዜና ከሐዋሳ በተፈጠረው አደጋ ችግር ውስጥ የሚገኙት የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ሁለት ባልደረቦች ማለትም ስራአስኪያጁ ጋዜጠኛ ሚሊዮን ደግነው ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ዋና አዘጋጁ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ከትላንትና ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ለገጣፎ አስተዳደር መታሰራቸውና እስከዛሬ ፍ/ቤት እንኩዋን አለመቅረባቸው መነጋገሪያ ሆኖአል፡፡ ጋዜጠኛውን ለመርዳት የምትፈልጉ ወገኖች በ0031687154530 ብትደውሉ ተጨማሪ መረጃ  የምታገኙ መሆኑን ለማስታወስ እንወዳለን።