የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወላጅ እናት ወ/ሮ ፋናዬ ልጃቸውን እንዳይጎበኙ እገዳ እንደተጣለባቸው አስታወቁ

ኢሳት (ታህሳስ 26 ፥ 2009)

በእስር ላይ የሚገኘው የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወላጅ እናት ልጃቸውን እንዳይጎበኙ እገዳ እንደተጣለባቸው አስታወቁ።

ይህንኑ እገዳ አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እኛ ለሌሎች አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ደብዳቤን የጻፉት ወ/ሮ ፋናዬ ይርዳቸው ከጉብኘት እገዳው በተጨማሪ የልጃቸውን ጤንነት ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን በደብዳቤያቸው አስነብበዋል።

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የጤንነት ሁኔታ እየተባባሰ መምጣትን ተከትሎ ጋዜጠኛው በቅርቡ ከሚገኝበት የዝዋይ እስር ቤት ወደ ባቱ ሆስፒታል መወሰዱ ይታወሳል።

ይሁንና ወ/ሮ ፋናዬ የልጃቸውን ሁኔታ ከሰሙ በኋላ ወደ ዝዋይ እስር ቤት ለጥየቃ ቢያቀኑም፣ የክልከላ እገዳ መጣሉን ማወቅ እንዳልቻሉና የልጃቸውን ሁኔታ ሳያውቁ መመለሳቸውን በደብዳቤያቸው አመልክተዋል።

በልጃቸው የጤንነት ሁኔታ ሃሳብ ገብቷቸው እንደሚገኙ የገለጹት ወ/ሮ ፋናዬ መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጉዳይን በጥሞና በመመልከት ሰብዓዊ ምላሽ እንዲሰጧቸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

ከሁለት አመት በፊት ለእስር የተዳረገው ጋዜጠኛ ተመስገን ከሳሽ አቃቤ ህግ ባቀረበበት የስም ማጥፋት ክስ ጥፋተኛ ተብሎ የሶስት አመት የእስር ቅጣት እንደተላለፈበት ይታወሳል።

ከሁለት አመት በፊት ለእስር የተዳረገው ጋዜጠኛ ተመስገን ከሳሽ አቃቤ ህግ በቀረበበት የስም ማጥፋት ክስ ጥፋተኛ ተብሎ የሶስት አመት የእስር ቅጣት እንደተላለፈበት ይታወሳል። አለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋማት በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኛ ተመስገንን ጨምሮ 16 ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙ ይገልጻል።

ሲፒጄ የ2016 አም ሪፖርቱን በቅርቡ ባቀረበ ጊዜ ኢትዮጵያ በርካታ ጋዜጠኞችን ለእስር በመዳረግ በአለም ካሉ ሃገራት መካከል ዋነኛ መሆኗን አመልክቷል።

የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ማክሰኞ ባስተላለፈው የፍርድ ውሳኔ በጋዜጠኛ ካሊድ መሃመድና ዳርሴማ ሶሪ ላይ ከአራት አመት በሚበልጥ የእስር ቅጣት ሰጥቷል። ይሁንና አለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች የእስር ቅጣት የሚጣልባቸው ጋዜጠኖች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል።