የጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ ህይወት አደጋ ላይ መሆኑ ተገለፀ፤ እንዲሁም በሰማያዊ ፓርቲ አባል አቃቤ ህግ ምስክር አሰማ

ታኀሳስ ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶበት የሶስት ዓመት እስር የተበየነበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ደህንነቱ አደጋ ላይ መውደቁን  ቤተሰቦቹ ገለፁ፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን፣ በዝዋይ ወህኒ ቤት፤ ኮማንደር ቢኒያም ተብሎ በሚጠራው የወህኒ ቤቱ አስተዳዳሪ ጠዋትና ማታ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰበት ከመሆኑም በላይ በቀን ለአምስት ጊዜ ያህል ሌሊትን ጨምሮ በሰበብ አስባቡ ከክፍሉ እየተጠራ ይወሰዳል፡፡

ቤተሰቦቹ እንዳሉት፦ጋዜጠኛ ተመስገን፣ በኮማንደር ቢኒያም እየተጠራ “እንገልሃለን፣ ከዚህ አንተ ሳይሆን ሬሳህ ነው የሚወጣው” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ ነው እየደረሰበት ያለው፡፡

በተመስገን ላይ በእስር ቤት ውስጥ  ዛቻውና ማስፈራሪያው እየጠነከረ የመጣውም በቅርቡ ለንባብ ባበቃው “የኢትዮጵያ መንግስት ገመና” በሚለው መጣጥፉ  ምክንያት እንደሆነ ቤተሰቦቹ መናገራቸውን የፍኖተ-ነጻነት ዘገባ ያመለክታል።

ተመስገን ከተያዘው ሳምንት ጀምሮም ምግብ እንዳይገባለት፣  በቤተሰብ፣ በወዳጅ -ዘመድ  እና በስራ በባልደረቦቹ እንዳይጎበኝ ከመደረጉም በላይ ለህይወቱ አስጊ በሆነ ሁኔታ ቀዝቃዛ መሬት ላይ እንዲተኛ  እየተደረገ ይገኛል።

ጋዜጠኛ ተመስገን፣ ፍትህ ጋዜጣ ላይ በፃፋቸው ፅሁፎች የተነሳ የሶስት ዓመት እስር ተበይኖበት ከወርሃ ጥቅምት ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል ‹‹መንግስትን የሚቃወም ወረቀት ሲበትን ይዘነዋል› የሚል ክስ ተመስርቶባቸው በእስር ላይ በሚገኙት በሰማያዊ ፓርቲ አባል ላይ አቃቤ ህግ  ምስክር አሰምቷል። የአቃቤ ህግ ምስክር የተሰማባቸው የሰማያዊ ፓርቲ አባል ፤ህዳር 27 እና 28/2007 ዓ.ም በ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ተዘጋጅቶ ለነበረው የአዳር ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ የቅስቀሳ በራሪ ወረቅት በመበተናቸው  ለእስር የተዳረጉት  አቶ ሲሳይ ዘርፉ ናቸው።

‹‹…‹ነጻነት ለፍትሓዊ ምርጫ› ለመላው ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ሁሉ….ተብሎ የተጻፈበት በራሪ ወረቀቶች ለህብረተሰቡ ሲያከፋፍል እጅ ከፈንጅ በመያዙ ፤ በፈጸመው የሐሰት ወሬን በማውራት ህዝቡን ማነሳሳት ወንጀል ተከሷል…›› የሚል ክስ፤ በፌዴራል አቃቤ ህግ በተመሰረተባቸው አቶ ሲሳይ  ላይ  ታህሳስ 30 ቀን 2007 ዓመተ ምህረት- ሁለት የአቃቤ ህግ ምስክሮች ቀርበው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ጉዳዩን ባስቻለው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት  የአቃቤ ህግ የመጀመሪያ ምስክር ሆነው የቀረበው ኮንስታብል ያለው መንግስቴ፣ ‹‹ተከሳሹን ህዳር 24 ቀን 2007 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ላይ መንግስትን የሚቃወም በራሪ ወረቀት ሲበትን አይተነዋል፤ በዚህም ወረቀት ሲበትን ያገኛችሁትን ሰው ያዙ ተብልን ስለነበር ተከሳሹን በቁጥጥር ስር አውለነዋል›› ብሏል፡፡

መስካሪው በወቅቱ ተከሳሹን ሲይዙት የፖሊስ ደንብ ልብስ እንዳልለበሱና በሲቪል እንደነበሩ ጠቅሶ፣ ‹‹የሚበተነው ወረቀት በዘጠኙ ፓርቲዎች መዘጋጀቱን እንጂ ይዘቱን አላስታውሰውም፤ የህግ አስከባሪ እንደመሆኔ ግን ተከሳሹን በቁጥጥር ስር እንዲውል አድርጌያለሁ›› ሲል መስክሯል።

ሁለተኛ የአቃቤ ህግ ምስክር ሆኖ የቀረበው ኮንስታብል ማርክሽ ሹመሌ በበኩሉ፣ ‹‹ሲቪል ነበር የለበስኩት፤ ተከሳሹ ወረቀት ሰጠኝ፡፡ ሳየው መንግስትን የሚቃወም ወረቀት ነው፡፡ ወረቀቱን ለጓደኛዬ አሳየሁት፡፡ ከዚያም በቁጥጥር ስር አዋልነው› ሲል የምስክርነት ቃሉን ሰጥቷል።

አቃቤ ህግም ሁለቱ ምስክሮች የሰጡትን ምስክርነት ከተያዘው በራሪ ወረቀት ጋር አገናዝቦ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲሰጥለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ ተከሳሽ አቶ ሲሳይ በበኩላቸው ‹‹መንግስትን መቃወም ህገ-መንግስታዊ መብቴ ነው፡፡ ስለሆነም ወንጀል አልሰራሁም›› ሲል ተከራክሯል፡፡

ይሁንና ዳኛው በበራሪ ወረቀቱ ላይ የተጠቀሰውን ‹‹የኢህአዴግ መንግስት ያፍናል፣ ያጭበረብራል፣ ይገድላል…›› የሚሉትን ሀረጎች በማውሳት ድርጊቱ ወንጀል ስለሆነ ተከሳሹ መከላከል አለበት ሲሉ ውሳኔ አስተላልፈዋል።  በመሆኑም የሰማያዊ ፓርቲው አባል   አቶ ሲሳይ ዘርፉ   የሰነድ ማስረጃዎቻቸውን ጨምሮ መከላከያ ምስክሮቻቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ለጥር 7/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡