የጋሞ ጎፋ ዞን ተወላጆች የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ

ሐምሌ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ላለፉት 20 ቀናት ሲጓተት የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ዛሬ በአርባምንጭ የተካሄደ ሲሆን፣ ህዝቡ መንግስት አይካፈፍለን በማለት ቁጣውን ሲገልጽ ተሰምቷል። ጎታና ቱፋ ታድላ የተባለ ጸሃፊ የጋሞን ህዝብ የሚያንቋሽሽ መጽሃፍ ማዘጋጀቱን ተከትሎ፣ የአካባቢው ህዝብ መንግስት ጋሞን ከጎፋ ህዝብ ጋር ለማጋጨት ሆን ብሎ የተሸረበው ሴራ ነው በማለት ሲቃወመው ቆይቷል።
“የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ይመጣሉ፣ አርበኞች ግንቦት7 አርባምንጭ ገብቷል፣ እንዲሁም አሸባሪዎች እናንተን መጠቀሚያ ሊያደርጉዋችሁ ነው” የሚሉ ሰበቦች እየተሰጡ የተቃውሞው ሰልፍ ሲጓተት የቆየ ሲሆን፣ ህዝቡ በራሱ ጊዜ ፈንቅሎ ለመውጣት ሲዘጋጅ፣ የአካባቢው ባለስልጣናት ሰልፉን መፍቀዳቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በሰልፉ ላይ አንድ የአካባቢው ሹም ተገኝቶ ንግግር ለማድረግ ሲሞክር ህዝቡ፣ “አንተን አንፈልግም፣ አለቆችህ ከላይ ይምጡልን” በማለት ተቃውሞ ያሰማ ሲሆን፣ አብዛኛው ህዝብ የጠየቀውን ባለማግኘቱ ንግግሩን ሳያዳምጥ ወደ ቤቱ ተመልሷል።
ጻሃፊው በቁጥጥር ስር ውሎአል ተብሎ ቢነገርም፣ በ10 ሺ ብር ዋስ መፈታቱን ምንጮች ተናግረዋል።
አንዳንድ የጋሞ ተወላጆች እንደገለጹት፣ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት የጎፋን ህዝብ ከጋሞ ጋር ለማጋጨትና ጎፋን ራሱን ችሎ በዞን እንዲከለል ለማድረግ ቅስቀሳ ጀምረዋል። ለዘመናት ተከባብረው የኖሩ ህዝቦችን ለማለያየት ሴራ የሚሸርቡ ባለስልጣናት ለፍርድ እንዲቀርቡም ነዋሪዎች ጠይቀዋል። በጋሞ ጎፋ ዞን ከማንነት፣ ከመልካም አስተዳደር እና ከፍትህ ጋር በተያያዘ ካለፉት 4 አመታት ጀምሮ ተጠናክሮ የቀጠለው ተቃውሞ አልበረደም።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለፉት 3 ሳምንታት ከታሰሩ 120 ሰዎች መካከል 60 ዎቹ መፈታታቸው ታውቋል።