(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 2/2011)በጋምቤላ እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቃወምና የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን የለውጥ እንቅስቃሴ የሚያደናቅፉ አመራሮች ከስልጣን እንዲወርዱ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ነገ በሚኒሶታ ተጠራ።
የጋምቤላን ሁኔታ መንግስት ትኩረት እንዲሰጠው ጫና ለመፍጠር ታስቦ በተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በሚኒሶታና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲገኙ ጥሪ ተደርጓል።
በነገው ዕለት በሴን ፖል የሚኒሶታ ግዛት ምክር ቤት ህንጻ የሚደረገው የተቃውሞ ሰልፍ በጋምቤላ እየተካሄደ ያለው እስርና አፈና እንዲቆም የሚጠይቅ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ጋምቤላን እየመሩ የሚገኙት ባለስልጣናት የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የሚያደናቅፉ በመሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስዱ በነገው ሰልፍ እንደሚጠየቅ አዘጋጆቹ ለኢሳት ገልጸዋል።
ከሚኒሶታ በኋላ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሚገኝበት ዋሽንገተን ዲሲ ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚካሄድም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።