የጋምቤላ ወጣቶች ወይም በእነሱ አባባል ዳልዲሞች ከዶክተር አብይ አሕመድ ጋር መነጋገር እንፈልጋለን ሲሉ ጥሪ አቀረቡ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 14 ቀን 2010 ዓ/ም ) ወጣቶቹ ዛሬ በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ክልሉል እያስተዳደረ ያለው አካል ላይ ላዩን የለውጡ ደጋፊ በመምሰል፤ ከአዲሱ የዶክተር አብይ አስተዳደር ጋር መደመራቸውን በይፋ የሚገልጹ ወጣቶችን ማሰር ጀምሯል።
ወጣቶቹ ወይም ዳልዲሞቹ ሰሞኑን በጋምቤላ ተሳብሰበው ባወጡት መግለጫ፤ በሕወሓት የተፈጠረው እና በጣም ጨቋኝና በዝባዥ የሆነው የክልሉ ገዢ መደብ በቃል ደረጃ “ተደምሬያለሁ” እያለ በተግባር ግን ለዶር አብይ ድጋፍ ለማሳዬት የወጡ የጋምቤላ ወጣቶችን ማሰሩን በማውገዝ፣ የታሰሩት ወጣቶች በቶሎ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ፣ የክልሉ መስተዳደር አካላት ባለፈው ሀሙስ ነሀሴ 10ቀን 2010 ዓ.ም በዚሁ አለመግባባት ዙሪያ ከዳልዲሞ ወይም ከወጣቶች ጋር ስብሰባ ተቀምጦ ነበር።
ስብሰባውን ተከትሎ አንድ ዳልዲም ታፍኖ መገደሉን የጠቀሱት ነዋሪዎች፤ በዚህ ወጣት መገደል ምክንያት በርካታ ወጣቶች ተቃውሟቸውን እና ቁጣቸውን እያሰሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ልጁን የገደሉበት ምክንያት ወጣቱ ጨቋኙን የክልሉን አስተዳደር እንዳይታገል ለማስፈራራት እና አካባቢውን ወደ ግርግር በማስገባት ዶክተር አብይ ሀገር ማረጋጋት ተስኖታል የሚለውን የአለቆቻቸውን ትዕዛዝ ላማስተላለፍ ነው የሚሉት የጋምቤላ ወጣቶች፣ እየተወሰደብን ያለው የኃይል እርምጃ የመብት ጥያቄ ከማንሳት እና የታሰሩት ወጣቶች እስኪፈቱ ድረስ ከምናደርገው ትግል አያግደንም ብለዋል።
በድጋሚ ማረጋገጥ የምንፈልገው ሀቅ ቢኖር እኛ ዳልዲሞች ዶክተር አብይ የለውጥ እርምጃ ደጋፊዎች መሆናችንን ነው ያሉት ዳልዲሞቹ፣ የለውጥ እንቅፋት በሆነው የክልሉ መስተዳድር ተግባራትና እየፈጸመብን ባለው በደል ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያነጋግሩን እንሻለን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።