የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አርነት ግምባር / ጋህዴአግ/ የኦህዴድን የግዛት ማስፋፋት ጥያቄን እንደሚያወግዝ አስታወቀ

ኢሳት ዜና ሰኔ 29 2009   

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት / ኦህዴድ / ከጋምቤላ ክልል ጋር በተያያዘ እያካሄደ ያለውን  ማስፋፋት ጥያቄ እንደሚያወግዝ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አርነት ግምባር / ጋህዴአግ / ባወጣው መግለጫ አስታወቀ ።

በአሁኑ ጊዜ የኦሮሞም ሆነ የጋምቤላ ህዝብ አንገብጋቢ ጥያቄ የግዛት መስፋፋት አለመሆኑን  ጋህዴአግ  ገልጿል ።

የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አርነት ግንባር /ጋህዴአግ/ በመግለጫው እንዳለው ህውሃት መራሹ ገዢ ግምባር ለዘመናት በሰላምና በመቻቻል አብሮ የኖረውን ህዝብ እርስ በእርስ እንዲጋጭ በማድረግ የአብሮነት ማህበራዊ እሴትን በመናድ ላይ ይገኛል ።

በተለይም በቅርቡ  በጋምቤላ አካባቢ የኦህዲድ መልክተኞችን በመላክ የድንበር ማስፋፊያ ጥያቄ መቅረቡ የዚሁ ደባ ማሳያ ነው ብሏል ።

ጋህዴአግ በመግለጫው ይህም የተደረገው የኦሮሞ እና የጋምቤላ ህዝብን ሆነ ብሎ ለማጋጨት ስለሆነ በእጅጉ እናወግዘዋለን ሲል ግንባሩ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል ።

እንደመግለጫው የኦሮሞም ሆን የጋምቤላ ህዝብ የወቅቱ ጥያቄ የፍትህ ፥ የዲሞክራሲ እና የነጻነት እንጂ የተሰፋፊነትና የድንበር አይደለም ።

እናም የሁለቱ ክልልሎች ህዝቦች የኦህዴድን የግዛት መስፋፋት ጥያቄ እንዳይቀበሉትና እንዲታገሉት የጋምቤላ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ አርነት ግንባር /ጋህዴአግ / ጥሪ አቅርቧል ።

የሁለቱም  ክልሎች ህዝብ በመተማመን በእኩልነትና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ድርጅቱ አጥብቆ እንደሚሰራም አስታውቋል ።