ኢሳት (ሚያዚያ 10 ፥ 2008)
አርብ እና ቅዳሚየ የተፈጸመውን የጋምቤላውን ጭፍጨፋ አለም አቀፍ ብዙሃን እየዘገቡ ነው። ኒው ዮርክ ታይምስ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው፣ ባለፈው አርብና ቅዳሜ ከ80 በላይ ቁስለኞች በጋምቤላ ሆስፒታል መድረሳቸውንና፣ አብዛኞቹ ጉዳተኞች በሰውነታቸው ውስጥ ጥይት እንዳለባቸው ዘግቧል። ሆስፒታሉም ከአቅሙ በላይ በቁስለኞች ስለተጥለቀለቀ፣ አብዛኞቹ ተጎጂዎች በሆስፒታሉ በረንዳ ላይ ተኝተው እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል ሲል ጋዜጣው ለንባብ አብቅቷል።
ክላሺንኮብ መሳሪያ ያነገቡና የወታደራዊ ደንብ ልብስ የለበሱ ጥቃት አድራሾች ፣ ጂካውና ላሬ በሚባሉ አካባቢዎች እንደደረሱ መንደሮችን በመክበብ ህጻናትና እናቶችን ጭምር ያለርህራሄ እንደጨፈጨፉ የአይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
እነዚህ ጥቃት አድራሾች የሙርሌ ብሄረሰብ አባላት ሲሆኑ ከዚህ በፊት ከብት መዝረፍ እንጂ እንዲህ አይነት አሰቃቂ ጥቃት አድርሰው እንደማያውቁ ጋዜጣው የጥቃቱ ሰለባዎችን አነጋግሮ አስነብቧል።
ልጁ ተጠልፎ የተወሰደበት አንድ የአይን እማኝ ለኒው ዮርክ ታይምስ እንደገለጸው ታጣቂዎቹ ከብቶቻቸውን መውሰድ እየቻሉ፣ ይህንን ሁሉ ጥቃት ለምን ማድረስ ፈለጉ ሲል በመገረም ጠይቋል።
እንደ አይን እማኞች ገለጻ፣ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚደንት ሳልባ ኪር ወገኖች የሆኑ የዲንቃ ብሄረሰብ አባላትም በጋምቤላው ጥቃት ተሳታፊ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል። የጥቃቱ ሰለባዎች ቀድሞ በደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩትና በኋላም የአማጺ ቡድኑ መሪ የሆኑት የሪክ ማቻር ኑዌር ጎሳዎች እንደሆኑ ጋዜጣው ዘግቧል።
እንደ ኒው ዮርክ ታይምስ ትንተና፣ ግድያው ምን አልባትም በፕሬዚደንት ሳልባ ኪር ትዕዛዝና ይሁንታ ተፈጽሞ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
ሚስተር ሪክ ማቻር ከሶስት አመት ስደት በኋላ በዛሬው እለት ወደ ደቡብ ሱዳን ተመልሰው በምክትል ፕሬዚደንትነት ለማገልገል ቃለመሃላ ይፈጽማሉ ተብሎ ይጠበቃል። የአሁኑ በኑዌሮች ላይ የደረሰው ጥቃት ግን ከሚስተር ማቻር ወደ ደቡብ ሱዳን መመለስ ጋር ይያያዝ አይያያዝ የታወቀ ነገር የለም።