የካቲት 1 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የጋምቤላውን ከፍተኛ ባለስልጣን አስገድለዋል የተባሉ አንዳንድ ባለስልጣናት መያዛቸው ተሰማ፣ ሶስት ባለስልጣናትን ለመግደል እቅድ ነበራቸው ተብሎአል
የኢሳት የጋምቤላ ወኪል እንደገለጠው በቅርቡ በክልሉ የተካሄደውን ግምገማ ተከትሎ በስውር የደህንነት አባል ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን አቶ ጌታቸው አንኮሬን ያስገደሉት የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ናቸው።
ግለሰቡ የከምባታ ተወላጅ ሆነው የህወሀት ሰላይ በመሆን የክልሉ ነዋሪዎችን ሲያሰቃዩ፣ እርስ በርስ ለመከፋፈል ሲሞክሩ መቆየታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።
አቶ ጌታቸው የተለያዩ የግንኙነት መስመሮችን በመዘርጋት በተወላጆች ላይ ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋት ፈጥረው እንደ ነበር መረጃዎች አመልክተዋል።
አቶ አንኮሬ ከክልሉ ፕሬዚዳንት መኖሪያ ግቢ ስብሰባ ጨርሰው ወደ ቤታቸው ሲሄዱ በበርካታ ጥይቶች ተደብድበው መገደላቸው ይታወሳል።
ጥቃቱን የፈጸመው ከስራ የተቀነሰ ነባር የፖሊስ አባል ሲሆን፤ የአካባቢው ባለስልጣናት ዩኒፎርም አልብሰው አስርገው በማስገባት ሶስት ባለስልጣኖችን እንዲገድል ትእዛዝ ሰጥተውት እንደነበር ለማወቅ ተችሎአል።
እንዲገደሉ የተባሉት ሁለቱ ባለስልጣናት ለምን እንዳልተገደሉ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። በአካባቢው በብዛት የሰፈሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት ግድያውን ፈጽሟል የተባለውን ፖሊስና አንድ የወረዳ ባለስልጣን በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ታውቋል።
በአካባቢው አሁንም ከፍተኛ ውጥረት ያለ ሲሆን፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት መንገድ ላይ ያገኙነት ሁሉ እያስቆሙ ይፈትሻሉ።
የክልሉ ተወላጆችና ባለስልጣናት ተወልደው ካደጉበት ቀየ ያለፍላጎታቸው በሰፈራ ስም እንዲፈናቀሉ መደረጉን እንደሚቃወሙት የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ለአቶ መለስ መንግስት ታማኝ በመሆን ነዋሪዎችን ያለፍላጎታቸው እንዲፈናቀሉ በሚያደርጉ ባለስልጣናት ላይ ነዋሪዎች እርምጃ መውሰድ መጀመራቸው ያስደነገጣቸው የክልሉ ባለስልጣናት ፣ ልዩ ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑም ተመልክቷል።
በጋምቤላ የሚፈጸመው የህዝብ መፈናቀል ከፍተኛ ተቃውሞ እየቀረበበት መሆኑ ይታወቃል።
አቶ መለስ ዜናዊ ትናንት በጋምቤላ ዙሪያ ከፓርላማ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ በጋምቤላ የሚካሄደውን የሰፈራ ፕሮግራም የሚቃወሙት ከመንግስት ጋር የርእዮት አለም ልዩነት ያላቸው ሰዎች ናቸው በማለት አድበስብሰው አልፈውታል።