ኢሳት (ጥር 12: 2009)
በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋምቢያ ባለፈው ታህሳስ በተደረገው አገር-አቀፍ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የተሸነፉት ያህያ ጀሜህ፣ ስልጣናቸውን ለአሸናፊው አዳማ ባሮው እንዲያስረክቡ የምዕራብ አፍሪካ መሪዎች ማግባባታቸውን ቀጥለዋል።
የጊኒው ፕሬዚደንት አልፋ ኮንዴ እና የማውርታኒያው ፕሬዚደንት ሞሃመድ ኦልድ አብደል አዚዝ ከሚስተር ጃሜህ ጋር ለመነጋገር ባንጁል እንደሚገኙ ታውቋል።
ያህያ ጀምህ ከስልጣን የሚለቁበትን ቀነ-ገደብ ዓርብ ከሰዓት በኋላ ያበቃ ሲሆን፣ ከስልጣናቸው በፈቃደኝነት የማይወርዱ ከሆነ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ጥምር የጦር ሃይል በሃይል ሊባረሩ እንደሚችሉ ተገልጿል።
የውይይቱ ውጤት እስኪታወቅ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገፈው የምዕራብ አፍሪካ አገራት የጦር ሃይል እንቅስቃሴውን እንዲገታ እንደተደረገም ለማወቅ ተችሏል። የምዕራብ አገራት ኢኮኖሚ ኮሚሽን ሊቀመንበር ማርሰል አላይን ደ ሶዛ ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ሚስተር ጃሜህ ከሁለቱ ፕሬዚደንቶች ጋር የሚደረገው ውይይት ካልተሳካ፣ ወታደራዊ ዕርምጃ እንወስዳለን ሲሉ ተናግረዋል።
አዳማ ባሮው በበኩላቸው ሃሙስ ዕለት በጎረቤት አገር በሴኔጋል ዳካር በሚገኘው የጋምቢያ ኤምባሲ ቃለ-መሃላ ከፈጸሙ በኋላ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ በጋምቢያ የስልጣን ሽግግር እንዲደረግ ድጋፍ እንዲሰጥ ተማጽነዋል።
በመፈንቅለ መንግስት ለ23 አመት በስልጣን ላይ የቆዩት ያህያ ጃሜህ፣ ባለፈው ታህሳስ ወር በተደረገው ምርጫ ሽንፈታቸውን ከተቀበሉ በኋላ፣ ምርጫው ስለተጭበረበረ በድጋሚ መደረግ ይኖርበታል በማለት ከስልጣን እንደማይወርዱ አስታውቀው ነበር።
ከምዕራብ አፍሪካ አባል ሃገራት (ECOWAS) የተውጣጣው የጦር ሃይል የጋምቢያን የምርጫውን ውጤት ለማስጠበቅና የጋምቢያን ህዝብ ድምጽ ለማስከበር አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ሃይል እንደሚጠቀም ተገልጿል። አንድ የሴኔጋል የጦር አዛዥ እንደገለጹት የየብስ፣ የባህርና የአየር ግብዓቶች መዘጋጀታቸውን ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ቃለ-መሃላ የፈጸሙትን አዳማ ባሮውን በመደገፍ አገሪቷ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንድታደርግ በሙሉ ድምጽ ድጋፍ ሰጥቷል።
ለተባበሩት መንግስታት የእንግሊዝ ረዳት አምባሳደር የሆኑት ፒተር ዊልሰን “የጋምቢያ ህዝብ በታህሳስ ምርጫ ድምፁን አሰምቷል። አዳማ ባሮውን ፕሬዚደንታቸውን አድርገው መርጠዋል፣ ድምጻቸው መሰማት አለበት” ማለታቸውን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት የአስቸኳይ ጊዜ ያወጁት ያህያ ጃሜህ፣ ፓርላማውን ሰብስበው ለተጨማሪ 3 ወራት የፕሬዝደንታዊ ስልጣናቸውን ማራዘማቸው ይታወሳል።
የጋምቢያ ምርጫ ከተደረገ በኋላ ሊከተል የሚችለውን የፖለቲካ ቀውስ በመፍራት ከ26ሺ ሰዎች በላይ ከጋምቢያ ወደ ሴኔጋል መሸሻቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ምክር ቤት ገልጿል።