ኀዳር ፲ (አስር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኦሮምያ ክልል በጉጂ ዞን የሚኖሩ የተለያዩ ብሄረሰቦች በአንድ ላይ በመሆን ያቀረብነው የመልካም አስተዳደር እና የፍትህ ጥያቄ ካልተመለሰ የህዝባዊ እምቢተኝነት ተቃውሞአቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
የዞኑ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና የአካባቢው ባለስልጣናት በአንድነት ሆነው ኦሮምያ ክልል በመሄድ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ መልስ ሊያገኙ አልቻሉም። ጥያቄያቸውን ይዘው ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ማምራታቸውንም ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ለኢሳት ገልጸዋል። አስተባባሪዎች ጥያቄያችን ካቀረብን 12 አመታት ቢሆነንም፣ እስካሁን መልስ አልተሰጠንም ይላሉ። በአስተዳደር አከላለል ችግር ምክንያት የዞኑ ነዋሪዎች በተለይም 6 ወረዳዎች ጉዳዮችን ለማስፈጸም እስከ 300 ኪሜ እየተጓዙ መሆኑን በመግለጽ፣ የ አስተዳደር አከላለሉ እንዲስተካከል ጠይቀዋል።
የሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ንብረት እንደሆነ በሚነገረው የኦኮቴ ወርቅ ማእድን ምክንያት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች አስፈላጊው ካሳ እንዲከፈላቸው፣ በተለያዩ ምክንያቶች የታሰሩ ወጣቶች እንዲፈቱም ጥያቄ አቅርበዋል።
ከ50 ሺ በላይ ህዝብ የፈረመበት ፊርማ ተሰባስቦ ለጠ/ሚኒስትሩ ገብቷል። በአንዳንድ የዞኑ ወረዳዎች ወጣቶች ውጭ በማደር ተቃውሞ ማሰማት መጀመራቸውንም የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ጉጂና ቦረና ወንድማማች ህዝብ ቢሆኑም መንግስት ጥያቄውን ላለመመለስ ህዝብ ከህዝብ ለማጋጨት እየሰራ መሆኑን የረባና ገዳ ባህላዊ መሪ እና የኮሚቴው አባል የነበሩት አቶ ቱኩና መሎ ተናግረዋል።
በአገር ቤት ከሚገኙ ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተሉ ስማቸውን ለደህንነት ስንል ከማንገልጻቸው ሰው ጋር እንዲሁም የችግሩን ምንጭ አንስቶ ታሪካዊ አመጣጡን እንዲያስረዱን አቶ ቱኩና መሎን አነጋግረናቸዋል። ከዜናው በሁዋላ ይቀርባል።