(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 30/2010) በጉራጌ ዞን ተከስቶ ከነበረው ህዝባዊ አመጽ ጋር በተያያዘ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ከስልጣን መነሳታቸው ታወቀ።
አስተዳዳሪው አቶ መሀመድ ኮርንማ የዞኑን ጸጥታ ማስከበር አልቻሉም ተብለው ከስልጣናቸው እንዲነሱ መደረጉንም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የአስተዳዳሪው መነሳት በይፋ የተገለጸ እንዳልሆነም ታውቋል።
በጉራጌ ዞን በተለይም በወልቂጤ ከተማ ለ8ቀናት የስራ ማቆም አድማና የአደባባይ አመጽ በተካሄደ ጊዜ ሶስት ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ነው።
የገዢው ፓርቲ አባላትና አንዳንድ አመራሮች አመጹን ትደግፋላችሁ ተብለው ከስራ መባረራቸውም የሚታወቅ ነው።
የቆየ ብሶት፣የተጠራቀመ በደል፣ የተከመረ ስቃይ የተገለጸበት የቅርብ ጊዜው የጉራጌ ተቃውሞ የጥሞና ጊዜ ላይ ይገኛል።
በተደራጀና ሁሉንም የጉራጌ አካባቢዎች ባዳረሰ መልኩ ተቃውሞውን ለመጀመር የጉራጌ ወጣቶች ዝግጅት ላይ ባለቡት በዚህን ወቅት አገዛዙ በባለስልጣናት ላይ ርምጃ መውሰዱ ነው የተሰማው።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ኮርንማ በቀጥታ ከህዝባዊ ተቃውሞው ጋር በተያያዘ ከስልጣናቸው መነሳታቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
አስተዳዳሪውን ከሃላፊነት ለማንሳት ለጊዜው የተሰጠው ምክንያት የዞኑን ጸጥታ በማስከበር ረገድ ደካማ አፈጻጸም አስመዝግበዋል በሚል ነው።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ ግን በአብዛኛው የጉራጌ ባለስልጣናት ላይ የቀረበው ግምገማ ከህዝባዊ ተቃውሞ ጀርባ እጃችሁ አለበት የሚል ነው።
ከወልቂጤው አመጽ በኋላ በዞኑ የድርጅት ሃላፊዎች ሰብሳቢነት በተደረገ ግምገማ በስም እየተጠቀሱ ባለስልጣናቱ አመጹን ሲደግፉት እንደነበረ መገለጹን የኢሳት ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ይሁንና ዋና አስተዳዳሪው ከስልጣን ለመነሳታቸው ይህ እንደምክንያት ቢቀርብ ከፖለቲካ አንጻር ዋጋ ያስከፍላል በሚል ሌላ ሰበብ እንደተሰጠው ተገልጿል።
የአስተዳዳሪው ከስልጣን መነሳት በክልሉም ሆነ በብሄራዊ መገናኛ ብዙሃን አለመገለጹን የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች የፖለቲካ ሁኔታው ታይቶ ውሳኔውን ለመቀየር በሚል የአስተዳዳሪው መነሳት እንዲደበቅ መደረጉን ይገልጻሉ።
ከዋና አስተዳዳሪው በፊት ሌሎች በታች እርከን የሚገኙ የዞኑ ሃላፊዎችም ከቦታቸው መነሳታቸው ታውቋል።
በጉራጌ ዞን በአገዛዙ እየተወሰደ ያለው ርምጃ የጉራጌ ወጣቶች የዘርማዎች ትግል ውጤት እንደሆነም እየተነገረ ነው።
ከአንድ ሳምንት በላይ በቆየው የወልቂጤው አድማ ንግድ ቦታዎችና የመንግስት ተቋማት ሲዘጉ የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ የተቋረጠ ሲሆን በህዝቡ በተወሰደ ርምጃ የዞኑ ገቢዎች ቢሮ ህንጻ መቃጠሉ የሚታወስ ነው።
በወቅቱም የሶስት ሰዎች ህይወት መጥፋቱም ይታወቃል።
አድማው ከወልቂጤ ሌላ በእንድብርና አገናም ተካሄዷል።
የጉራጌ ወጣቶች ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የነጻነት ትግሉን ለማካሄድ ቃል በመግባት ለተጠናከረ አመጽ በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የጉራጌ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ወደ አዲስ አበባ ይገባል የሚል ስጋት ያደረበት አገዛዙ ተቃውሞው ዳግም እንዳይቀሰቀስ ወታደራዊ ሃይሉ በመጠናከር ላይ መሆኑም ታውቋል።