ኀዳር ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ምንጮች እንደገለጹት ድርቁን ተከትሎ በምስራቅ ሃረርጌ አካባቢ በዘንድሮው አመት 75 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በርሃብ መጋለጡን የአካባቢው ባለስልጣናት እየገለጹ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት ሳምንታት ዘናብ ካልዘነበ፣ ህዝቡ ሙሉ በሙሉ ፈልሶ ወደ ሀረር ከተማ ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት ደቅኗል። አንዳንድ ሴቶችና ህጻናት ረሃቡን በመሸሽ ባቢሌ ከተማ መግባት ጀምረዋል። የአካባቢው ባለስልጣናት እንዲህ አይነት ድርቅ አይተው እንደማያውቁ እየገለጹ ነው።
በሌላ በኩል መንግስት በሚቀጥሉት 2 ወራት የተረጅው ቁጥር 10 ሚሊዮን 200 ሺ እንደሚደርስ አስታውቋል:የረሃቡ ሁኔታም አስከፊ ሆኖ እንደሚቀጥል መግለጫ ሰጥቷል። በምክትል ጠ/ሚኒስትር ደምቀ መኮንን የተሰጠው መግለጫ ከዚህ በፊት ጠ/ሚኒስትሩና አዲሱ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ጌታቸው ረዳ ሲሰጡት ከነበረው መግለጫ ለዘብ ያለና አለማቀፉን ማህበረሰብ የሚማጸን ነው። አቶ ጌታቸው ረዳ አለማቀፉ ማህበረሰብ እርዳታ ለማግኘት ሲል የተረጅዎችን ቁጥር አጋኖ ያቀርባል በሚል መናገራቸው በአግር ውስጥ ያሉ ለጋሽ አገራትን አደናግሮ ነበር። ይሁን እንጅ መንግስት አሁን በሰጠው መግለጫ፣ ለጋሽ አገራት እስካሁን ፈጥነው እርዳታ አለመስጠታቸው እንዳሳዘነውና እርዳታው በአስቸኳይ እንዲመጣ ጠይቋል።የተባበሩት መንግስታትና ሌሎች ለጋሽ አገራት የተራበውን ህዝብ ቁጥር 15 ሚሊዮን ያደርሱታል። ምንመ እንኳ መንግስት የ2 ወሩን ተረጅ ቁጥር ብቻ የጠቀሰ ቢሆንም፣ አሃዙ ይጨምራል የሚል ስጋት እንደገባው አልሸሸገም።
አደጋውን ለመቀነስ አለማቀፍ መንግስታት በኢትዮጵያ ድርቅ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ባለስልጣኖቹ ተማጽነዋል።
ከ2 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በረሃቡ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። በደንቢያ ፣በሰሜን ወሎ፣ ሶማሊ እና አፋር አካባቢዎች ዜጎች ስደት ጀምረዋል። መንግስት የሚያቀርበው 10 ኪሎ የወር ቀለብ ሊበቃቸው እንዳልቻለ ተረጅዎች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በህዳር ወር የምግብ ግሽበት ዋጋ ከአምናው ጋር ሲነጻጻር በ9.9 በመቶ ጭማሪ አሳዬ፤ የማእከላዊ ስታተስቲክስ ቢሮ ባወጣው ጥናት አጠቃላይ ተንከባላይ የምግብ ዋጋ ግሽበት 11 .7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበትም በ7.9 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
የህዳር ወር የምግብ ዋጋ ግሽበት ከአለፈው አመት ጋር ሲነጻጻር 11.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ይህ ወር ከአምናው ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጻር በዳቦና እህል ላይ 4.6 በመቶ፣ ስጋ 11.9 በመቶ፣ ወተት አይብና እንቁላል 21 በመቶ፣ ዘይትና ቅባቶች 11.2 በመቶ፣ ፍራፍሬ 22 ከመቶ እንዲሁም ሌሎች ምግቦች 41.8 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል።
ከአምናው ጋር ሲተያይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው ክልሎች አዲስ አበባ ፣ አፋር፣ አማራ፣ ጋምቤላና ኦሮምያ ናቸው። በምግብ በኩል ከፍተኛ ጭማሪ የታየባቸው ክልሎች አዲስ አበባ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና ኦሮምያ ናቸው።