(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 28/2009) የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የቀድሞ ዳይሬክተር ታሰሩ።
የመንግስትና የፓርቲ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ሁለቱ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር የዋሉት በሌብነት ወንጀል ተጠርጥረው ነው።
ፓርላማው ዛሬ አርብ ሐምሌ 28/2009 ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ ጉጆ ከፓርላማ ሲወጡ ወዲያው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
የመንገዶች ባለስልጣን የቀድሞ ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል ሐሙስ መታሰራቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ፓርላማው በሚያደርገው አስቸኳይ ስብሰባ በሌብነት የተጠረጠሩ የፓርላማ አባላትን ያለመከሰስ መብት እንደሚያነሳ ኢሳት የፖለቲካ ተንታኞችን በመጥቀስ ከሳምንቱ መጀመሪያ ጀምሮ ሲዘገብ ቆይቷል።
ሆኖም በሌብነት በፊውታራሪነት የሚጠረጠሩት አቶ አባይ ጸሃዬ እንዲሁም የቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሶፊያን አህመድ በግንባር ቀደምትነት በክሱ ዝርዝር ውስጥ እንደሚገቡ ቢጠበቅም ሕወሃት በደጋፊዎቹ ሰፈር በተፈጠረበት ጫጫታ የአቶ አባይ ጸሃዬ ያለመከሰስ መብት ሳይነሳ መቅረቱን የሚገልጹ ወገኖች አሉ።
የፖለቲካ አመራሩን በተመለከተ አቶ አባይ ጸሃዬን ሳይነኩ የኦህዴድና የብአዴን ባለስልጣናትን መንካት የብሔረሰብ ውጥረት በማስከተል የፖለቲካ ቀውስ ይፈጥራል በሚል እነ አቶ ሶፊያን አህመድን እንዳለፉዋቸውም ተገምቷል።
የፖለቲካ ውጥረት በበረታባቸው በኦሮሚያና በአማራ ክልል ባለስልጣናትን ለመንካት ያልደፈሩት የህወሃት ባለስልጣናት የደቡብ ክልል የደኢህዲን ሰዎች ላይ ያተኮሩ መስለው ተገኝተዋል።
በዚህም መሰረት እስካሁን ከታሰሩት ውስጥ በሚኒስትርና በሚኒስትር ዴኤታ ደረጃ ብቸኛ ሆነው የተገኙት በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ማይክሮ ፋይናንስ ሃላፊ የነበሩት አቶ አለማየሁ ጉጆ ናቸው።
አቶ አለማየሁ ጉጆ ዛሬ የታሰሩት ግን በሚኒስትር ዴኤታ ስልጣናቸው ላይ እያሉ ነው።