የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ችግሮችን ለመመርመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክርን ሊያካሄድ ነው ተባለ

ኢሳት (ሰኔ 30 ፥ 2008)

በመንግስት ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ ያስከተሉትን የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ጉዳይ ለመመርመር የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ፋብሪካዎቹን ለመገንባት ከተመረጡ አካላት ጋር ምክክርን ሊያካሄድ መሆኑን ገለጠ።

በ77 ቢሊዮን ብር ይገነባሉ የተባሉትና ከሶስት አመት በፊት ወደ ስራ ይገባሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩት ፋብሪካዎች ያሉበት ደረጃ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ሚኒስትሩ ለፓርላማ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ሃላፊዎች ፋብሪካዎቹን ለመገንባት ሃላፊነት ተሰጥቶት የነበረው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በግንባታው ሂደት ችግርን እንደፈጠረ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

ይሁንና ለፋብሪካዎቹ ወደስራ አለመግባት ተጠያቂው በአግባቡ ተለይቶ ባለመታወቁ ምክንያት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ሜቴክን ጨምሮ ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በችግሩ ዙሪያ ሊመከር መሆኑ ታውቋል።

መንግስት ለስኳር ፋብሪካዎቹ ግንባታ ከቻይና መንግስትና ከሃገር ውስጥ በብድር በማሰባሰብ ወደ 77 ቢሊዮን ብር መድቦ የፋብሪካዎች ግንባታ ቢጀመርም ኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ውስጥ መሆኑን ከወራት በፊት ለፓርላማ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

ፋብሪካዎቹ ምርት ማምረት ይጀምራሉ ተብሎ ሲጠበቅ የስኳር ኮርፖሬሽን የፋይናንስ እጥረት እንዳጋጠመው መግለፁ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማጋጠሙን ማሳያ እንደሆነ የመንግስት ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አቶ አብዱላዚዝ መሃመድ የፋብሪካዎቹ የፋይናንስ አፈጻጸም በአሳሳቢ ደረጃ ለይ መሆኑን ሰሞኑን ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል።

ፋብሪካዎቹ ወደስራ መግባት ባለመቻላቸው ምክንያት መንግስት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን በመመደብ በሃገር ውስጥ የተፈጠረን የስኳር እጥረት ለመቅረፍ ስኳርን ከህንድ በማስገባት ላይ መሆኑን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ሚኒስትሩ አቶ አብዱላዚል በስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ላይ ከታየው ችግር በተጨማሪ በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች ከፍተኛ ገንዘብ ተመድቦላቸው በመገንባት ላይ ያሉ የመንገድ ፕሮጄክቶች በጊዜ ያለመጠናቀቅና የጥራት ችግር እንዳለባቸው አክለው አስታውቀዋል።