የገናን በዓል አስመልክቶ በአዲስ አበባ የሽንኩርት ዋጋ ከወትሮው በተለየ መልክ ከፍተኛ ጭማሪ አሳየ፡፡

ታኀሳስ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሁሉም ዓይነት ሸቀጦች ላይ ጭማሪ መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ የሽንኩርት ግን ከወትሮው የተለየ መሆኑን
ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ተጠይቀውም “ከቦታው ስለማይገባ ነው” የሚል መልስ ከመስጠት ውጪ ዝርዝር ምክንያት ማቅረብ አልቻሉም፡፡ በዚሁ መሰረት የአበሻ ሽንኩርት በኪሎ ግራም ከ27 እስከ 30 ብር ፣ የፈረንጅ ከ10 እስከ 16 ብር ፣ ነጭ ሽንኩርት ከ50 እስከ 55 ብር በመሸጥ ላይ ነው፡፡
ዋጋው እንዲህ ከመናሩ በፊት የአበሻ ሽንኩርት ለረጅም ጊዜ በኪሎ 12 እና 13 ብር ሲሸጥ ነበር፡፡ የዶሮ ዋጋ ገበያ ለግምት አስቸጋሪ ዋጋ የሚጠራበት ሲሆን ወንድ ዶሮ ከ250 እስከ 600 ብር ፣ ሴት ዶሮዎች ከ 170 እስከ 400 ብር ዋጋ የሚጠየቅባቸው ሲሆን ፣ በግ ከ 1700 ብር እስከ 6500 ብር ዋጋ እየተጠራባቸው መሆኑን አስተውለናል፡፡ ፍየል ከ3500 እስከ 7000 ብር ዋጋ የሚያወጡ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡
አንድ የፈረንጅና የአበሻ እንቁላል ከብር 3 ከ60 እስከ 3ከ 85 ሳንቲም እየተሸጠ መሆኑ ታውቆአል፡፡ በሰሞኑ የበኣል ገበያ ከሽንኩርት መወደድ በስተቀር አብዛኛዎቹ ሸቀጦች ዋጋዎች ካለፈው በዓል ብዙም ለውጥ
እንደሌለው ተጠቃሚዎች ተናግረዋል፡፡ ይህም ሆኖ ዋጋዎቹ ከሸማቹ አቅም በላይ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡