የጃፓን መንግስት በሶማሊያ ክልል ለድርቅ ለተጠቁ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች የሚውል የ2 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ለዩኒሴፍ ለገሰ።

መጋቢት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የገንዘብ እርዳታው በዩኒሴፍ አማካኝነት ለውሃ፣ ለጤና፣ ለንጽህና አገልግሎቶች፣ ለተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እና ለአጣዳፊ የጠቅማጥ በሽታ መድሃኒት መግዣ እንደሚውልም ተገልጿል።
ድርቁን ተከትሎ ተላላፊ በሽታዎች በመዛመታቸው በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችን ሕይወት ለመታደግ ለንጽህና አገልግሎት 1.5 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል።የኢትዮጵያው ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ባቀረቡት አፋጣኝ የእርዳታ ጥያቄ ጥሪ መሰረት የጃፓን መንግስት እርዳታውን መስጠቱን በኢትዮጵያ የጃፓን አንባሳደር አስታውቀዋል። የጃፓን መንግስት እርዳታ ነዋሪዎቹ በንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ምክንያት ከሚከሰቱ ውሃ ወለድ በሽታዎች፣ አጣዳፊ ተቅማጥ የሚጋለጡትን ሕጻናት እና እናቶችን ሕይወት ይታደጋል።
አንባሳደር ሚሲንቺ ሳይዳ እንዳሉት ”እኛ የሰጠነው ረድኤት ለድርቅ ለተጎዱ ዜጎች በተገቢው መንገድ እንደሚደርሳቸው ተስፋ አለን። የጃፓን መንግስት በቀጣም ሕይወት የማዳን ስራዎች ላይ ይሳተፋል” ብለዋል።
በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ጋሊያን ማሌሶፕ በበኩላቸው ”በኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት ሕጻናት ክፉኛ ተጎጂ ሆነዋል። እነዚህ የድርቅ ተጠቂ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ አፋጣኝ ርብርብ ማድረግ አለብን። የጃፓን መንግስት በድርቅ ተጎጂ ሕጻናትን ሕይወት ለመታደግ አፋጣኝ ምላሽ መስጠቱ በጎነታቸውን ያሳል። በቀጠናው ከፍተና የሆነ ሰባአዊ ቀውስ ከመከሰቱ አስቀድሞ ለተጎጂዎች ልንደርስላቸው ይገባል።”በቀጠናው የርሃብ አደጋ እና በሽታ እየተዛመተ መምጣቱን ዩኒሴፍ አስታውቋል።