ዜና (የካቲት 2 ፥ 2009)
ኢትዮጵያና ጃማይካ በኢትዮጵያ የሚገኙ የጃማይካ ተወላጆች ዜግነት የሚያገኙበት ህጋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከር መጀመራቸውን የጃማይካ መገኛኛ ብዙሃን ሃሙስ ዘገቡ።
በጃማይካ ጉብኝትን እያደረጉ የሚገኙት በአሜሪካ፣ ጃማይካና፣ እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ ሃገራት የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ግርማ ብሩ ኢትዮጵያና ጃማይካ በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን እንዳስታወቁ ጃማይካ ኦብሰርቨር የተሰኘ ጋዜጣ አስነብቧል።
ወደ 500 የሚጠጉ የጃማይካ ተወላጆች በኢትዮጵያ በተለይ በሻሼመኔ ከተማ ዙሪያ ከ50 እና 60 አመት በፊት ጀምሮ እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይሁንና የጃማይካ ተወላጆች ለበርካታ ዘመናት በኢትዮጵያ ቢኖሩም የኢትዮጵያ ዜግነት ማግኘት እንዳልቻሉ ይነገራል። የኢትዮጵያ ህግ ድርብ ዜግነት የማይፈቅድ በመሆኑን የጃማይካ ተወላጆች ከ50 አመት በላይ የዜግነት ጥያቄያቸውን ህጋዊ ምላሽን ሳያገኝ መቆየቱ ታውቋል።
ይኸው ህጋዊ ክፍተት እልባት በሚያገኘበት ዙሪና የጃማይካ ተወላጆቹ የኢትዮጵያ ዜግነት በሚያገኙበት ዙሪያ በሁለቱ ሃገራት መካከል ምክክር እየተካሄደ መሆኑን የጃማይካው ጋዜጣ አምባሳደሩን ዋቢ በማድረግ በሪፖርቱ አስፍሯል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የጃማይካ ተወላጆች የሃገራቸውን ዜግነት እንደያዙ በኢትዮጵያ የሚኖሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ህጋዊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አምባሳድሩ አክለው አስረድተዋል።
በሁለቱ ሃገራት መካከል የተጀመረው ምክክር ዕልባት እስኪያገኝ ድረስም በኢትዮጵያ የሚገኙ የጃማይካ ተወላጆች አሁንም ያላቸውን ዜግነትና መታወቂያ ይዘው እንደሚቆዩ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ከ50 አመት በላይ እንደኖሩ የሚነገርላቸው የጃማይካ ተወላጆች በኖሩባቸው ጊዜያት ልጆችን በሃገሪቱ ቢወልዱም የዜግነት ህጋዊ ጥያቄዎች ግን ምላሽ አለማግኘታቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ድርብ ዜግነት የማትፈቅደው ኢትዮጵያ በቅርቡ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የነበራቸውን የአክሲዮን ድርሻ በመሰረዝ መብት እንዳይኖራቸው አዲስ ህግ ተግባራዊ ማድረጓ ይታወሳል።
የህጉን መውጣት ተከትሎም በባንኮች አክሲዮንን ገዝተው የነበሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድርሻቸውን እንዲመልሱ ተደርጎ፣ አክሲዮናቸው ለጨረታ ቀርቦ በመሽጥ ላይ መሆኑ ተዘግቧል።
በኢትዮጵያ ጥምር ዜግነት እንደማይፈቀድ በግልፅ በህግ በተቀመጠበት በአሁኑ ወቅት አቶ ግርማ ብሩ ስለ ጥምር ዜግነት ምልክት መስጠታቸው በምን ዓላማ፣ ማንን ለመጥቀም እንደሆነ ግልፅ አልሆነም።