ጥቅምት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የጀርመን መሪ አንጌላ ሜርክል በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ከፖለቲካ አፈና ወጥቶ ህዝቡ የሚሳተፍበትን መንገድ እንዲፈልግ እና የጸጥታ ኀይሎች ተቃውሞ በሚያሰሙ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የኀይል ርምጃዎች ከመውሰድ እንዲታቀቡ ጠይቀዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ከአንድ ዓመት በላይ የኾነው ፖለቲካዊ ቀውስ ከ500 በላይ ለሚኾኑ ንጹሃን ዜጎች ሞት ምክንያት ኾኗል ብለዋል።
ከጠቅላይ ሚንስትር ኀይለማሪያም ደሳለኝ ጋር በመኾን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ሜርክል ፣ ኢትዮጵያ የገቡት በመዲናይቱ አዲስ አበባ ዙርያ የተነሳው ትኩስ ተቃውሞ እና ግጭት በአገሪቱ ላይ ጥላውን ባጠላበት ማግሥት ነው።
የዐመጹ በፍጥነት መፋፋም ያስደነገጠው የኢሕአዴግ አገዛዝ እሁድ ዕለት በመላ አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ እንዲደነግግ አስገድዶታል። አገዛዙ የሰብዓዊ መብት ተሟጓች ድርጅቶች የሟች ዜጎችን አሃዝ አጋነው አቅርበዋል፣ “ነፍጥ ያነሱ የውጭ ኀይሎች” ያስነሱት ሁከት ነው በማለት ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን ለማጣጣል ሞክሯል።
ከፍተኛውን እርዳታ ለጋሽ የሆኑት የምዕራብ አገራት ካምፓኒዎቻቸው በድህነት ውስጥ በምትገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንቨስትምንት ጨረታዎችን ለማሸነፍ ቢፈልጉም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው በልማት ስም የሚደረገው የአገዛዙ አፋኝ አካሄድ አሳስቧቸዋል።
አንጌላ ሜርከል ”ችግር ካለባቸው አካላት ጋር ግልጽ የሆነ ውይይት መካሄድ አለበት።” በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የጸጥታ አስከባሪዎች የሚወስዷቸው የኀይል እርምጃዎች ተመጣጣኝ መኾን አለባቸው ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነግረዋቸዋል።
በዲሞክራሲ ምንጊዜም በፓርላማ ውስጥ የተቃዋሚ ድምጽ መኖር አለበት ሲሉ ያሉት መርከል፣ በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ስር በሚገኘው ፓርላማ ለመናገር የቀረበላቸውን ግብዣ ውድቅ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኀይለማሪያም ደሳለኝ በበኩላቸው “መንግሥት ለብጥብጥ መፈጠር ምንም ዓይነት የሃይል እርምጃዎችን አልወሰደም። ይህ ከሆነ ግን በጋራ ማጣራት እናደርጋለን” ሲሉ ወቀሳውን በማስተባበል ምላሽ ሰጥተዋል።