ሚያዝያ ፴ ( ሠላሳ ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፍቅር እስከመቃብርን ጨምሮ በርካታ ረዣዥምና ዘመን ተሻጋሪ ልቦለድ መጽሐፍትን ላበረከቱት ለታዋቂው ኢትዮጵያዊ ደራሲ ለክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማዬሁ በደብረማርቆስ ከተማ የተገነባውን ሐውልት የመረቁት የባህል ሚኒስትሯ ወረቀታቸው ጠፍቷቸው ንግግራቸውን ማቋረጣቸው ተሰማ።
ቅዳሜ ዕለት ሚያዚያ 28 ቀን 2009 ዓመተምህረት በተደረገው የመታሰቢያ ሐውልት ምርቃት ሥነ ስር ዓት ላይ የክብር እንግዳና ተናጋሪ የነበሩት ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት በጽሁፍ ካዘጋጁት ንግግራቸው አንደኛውን ገጽ ካነበቡ በኋላ ሁለተኛው ገጽ የጠፋቸው ሲሆን፤ ፈልገው ሊያገኙት ባለመቻላቸው ንግግራቸው ሊቋረጥ ችሏል።
ታዳሚው ያዘነው ንግግራቸውን ያሰፈሩበት ገጽ ከመጥፋቱ በላይ ፦”ማታ ነበር ጫር ጫር ያደረኩት ጠፋብኝ” ብለው እዚያው በአደባባይ እንደ ተራ ነገር መናገራቸው ነው ያሉት ምንጮች፤ ይህ ታላቁን ደራሲና መታሰቢያ ሐውልታቸውን ሊመርቅ በስፍራው የተገኘውን ሕዝብ መናቅ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሯ ወረቀቱን እንደጠፋቸው ከተናገሩ በኋላ በቃላቸው ገለጻ ለማድረግ ቢሞክሩም፤ የመናገር ልምዱ ስለሌላቸው ይሁን አለያም ስለክስተቱ በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸው፤ ንግግራቸውን ሳይጨርሱ አቋርጠው ለመውረድ ተገደዋል።
በስፍራው የነበሩት ታዳሚዎች ”ባለሥልጣኖች ለኛ እንኳ ክብር ባይኖራቸው ምናለበት የታላቁን የብርዕ ሰው ሃውልት ለማስመረቅ ሲመጡ ጥቂት እንኳ ቢዘጋጁ“ ሲሉ ተደምጠዋል።