የዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚደንታዊ በአለ ሲመት አርብ በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ እንደከበር ተገለጸ

ኢሳት (ጥር 11 ፥ 2009)

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አርብ በዚሁ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በሚካሄድ ደማቅ በአለ ሲመት የፕሬዚደንትነት ስልጣናቸውን እንደሚረከቡ ተልገጸ።

የአሜሪካ የጸጥታ ሃይሎች በዚሁ ስነስርዓት ወቅት ዝግጅቱን ሊያውል የሚችል ተቃውሞ ሊካሄድ ይችላል የሚል ስጋት በመኖሩ የጸጥታ ቁጥጥሩ ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ መጠናከሩን አስታውቀዋል።

በዚሁ በአለ ሲመት ላይ ለመታደም ከተለያዩ ግዛቶች በርካታ ሰዎች ወደ ዋና ከተማዋ በመግባት ላይ ሲሆኑ፣ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በዝግጅቱ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይሁንና ከምርጫ ቅስቀሳ ጊዜያቸው ጀምሮ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው የነበሩ ተመራጩ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በበአለ-ሲመታቸው ስነስርዓት ወቅትም ታላቅ ተቃውሞ ሊያስተናግዱ እንደሚችሉ የአሜሪካ የጸጥታ ሃይሎች ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ይህንኑ ተቃውሞ በመስጋት ከተለያዩ ግዛቶችና የጸጥታ አካላት የተውጣጡ ልዩ የጥበቃ አካላት የጸጥታ ቁጥጥርን እያካሄዱ ሲሆን፣ የዶናልድ ትራምፕ በአለ ሲመት ከዚህ ቀደም ከተከናወኑ ስነስርዓቶች ከፍተኛ የደህንነት ስጋት የታየበት መሆኑም ተነግሯል።

የዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የጸጥታ ሃላፊ የሆኑት ክርስቶፈር ጌልደርት በግለሰቦች ሊፈጸም የሚችል የደህንነት ስጋትን ጨምሮ በኢንተርኔት ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ጥቃቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

የአበአለ ሲመቱ አዘጋጆች በበኩላቸው ለጸጥታ ቁጥጥርና ተያያዥ ዝግጅቶች ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር (የአራት ቢሊዮን ብር) አካባቢ በጀት መደረጉን ገልጸዋል።

በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የሚገኙ አምስት ትላልቅ ሆስፒታሎች ከሙሉ ሰራተኞቻቸው ጋር በበአለ ሲመቱ እለት በልዩ ዝግጅት እንዲጠባበቁ የተደረገ ሲሆን፣ ከሃሙስ ጀምሮ በአለ ሲመቱ በሚከናወንበት ስፍራ ያሉ ዋና ዋና ጎዳናዎች ዝግ መደረጋቸውም ታውቋል።

በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ተቃውሞን ለማካሄድ ቅስቀሳን እያካሄዱ ያሉ አካላት በበኩላቸው የበአለ ሲመቱን ስነስርዓት ለማወክ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርጉ ይገልጻሉ።

የሃገር ውስጥ የጸጥታ ሃላፊ የሆኑት ጄ ጆንሰን በበኩላቸው የአሜሪካ ፖሊሶች እና ሌሎች ልዩ የደህንነት ሃይሎች ስነ-ስርዓቱን ለማወክ የሚደረጉ ጥረቶችን ለመከላከል በቂ ዝግጅት ማደረጋቸውን ለሮይተርስ አስረድተዋል።

በአለ ሲመቱ በተካሄደ ማግስት ቅዳሜ በዚሁ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በሴቶች አስተባበሪነት የተጠራ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።