የዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ ቀብር ነገ ማክሰኞ ይፈጸማል

ኢሳት (ግንቦት 8 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ለረጅም አመታት በአሰልጣኝነት ሲያገለግሉ የነበሩት ዶክተር ወልደ መስቀል ኮስትሬ ባደረባቸው ህመም እሁድ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።

የእኝሁ አንጋፋ አሰልጣኝ የቀብር ስነስርዓት ማክሰኞ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኝው የቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን እንደሚፈጸምም ታውቋል።

በ1942 ዓም በሰሜን ሸዋ ተጉለትና ቡልጋ የተወለዱትና ለኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት አባት የሚል መጠሪያ ያላቸው አንጋፋው አሰልጣኝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጤና እክል አጋጥሟቸው መቆየቱን የቅርብ ጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

በ69 አመታቸው እሁድ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ዶክተር ወልደ መስቀል ኮስትሬ ከ1984 ዓም ጀምሮ በዋና አሰልጣኝነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውም ታውቋል። ከሶስት አስርተ-አመታት በላይ በዘለቀው የአትሌቲክስ አገልግሎታቸውም አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴን ጨምሮ በርካታ አትሌቶችን ለአለም አቀፍ ድል እንዳበቁ ይታወቃል።

ባለፈው አመት ያጋጠማቸውን ህመም ተከትሎ ዶክተር ወልደ መስቀል ኮስትሬ የጭንቅላት ቀዶ ህክምና አካሄደው የነበረ ሲሆን፣ ይህንኑ ህመማቸውንም እስከ እለተሞታቸው ድረስ ሲከታተሉ እንደነበርም የቅርብ ጓደኞቻቸው ይገልጻሉ።

የእኚሁ ታላቅ አሰልጣኝ የቀብር ስነ-ስርዓት ነገ ማክሰኞ 9:00 ሰዓት እንደሚከናወን የተገለጸ ሲሆን፣ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት እንደነበሩም ከህይወታቸው ታሪክ ለመረዳት ተችሏል።