የድርቅ አደጋ እየደረሰባቸው ያሉ ወረዳዎች ቁጥር ከ200 በላይ ማሻቀቡን ተገለጸ

ኢሳት (ጥር 26 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ አዲስ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ጉዳት እየደረሰባቸው ያሉ ወረዳዎች ቁጥር ከ200 በላይ ማሻቀቡን የአለም ምግብ ፕሮርግራም (FAO) አስታወቁ።

በአራት ክልሎች በመዛመት ላይ ባለው በዚሁ የድርቅ አደጋ 86 ወረዳዎች ደግሞ ክትትልን የሚፈልጉ ተብለው በአንደኛ ደረጃ ተለይተው መቀመጣቸውን ድርጅቱ ድርቁን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል። የአለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በበኩላቸው የአለም ማህበረሰብ ችግሩን ለመታደግ አፋጣኝ ርብርብ በአውቅቱ ካላደረገ የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል አሳስበዋል።

ከባለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሊ እና ደቡብ ክክሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች በተከሰተው አዲስ የድርቅ አደጋ በአጠቃላይ 217 ወረዳዎች ለአደጋ መጋለጣቸው ተመልክቷል።

በአብዛኛው የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ንብረት የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት በመሞት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ወደ አንድ ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑ አርብቶ አደሮች ከዚህ ችግር ለመታደግ 20 ሚሊዮን ዶላር እንደሚፈልግ የአለም ምግብ ፕሮግራም ገልጿል።

በአጠቃላይ 5.6 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አዲስ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ተጋልጠው የሚገኙ ሲሆን፣ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

ይሁንና ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያስፈልገው ድጋፍ በአፋጣኝ መድረስ ካልጀመረ በአካባቢው የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ሊከስተ እንደሚችል የእርዳታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።

በድርቁ ሳቢያ ከግብርና ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ የአለም ምግብ ፕሮግራም ወደ 42 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልገው በሪፖርቱ አስፍሯል።

ባለፈው አመት በስድስት ክልሎች ተከስቶ የነበረው ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ ሙሉ ለሙሉ ዕልባት ሳያገኝ አዲስ የድርቅ አደጋ ማጋጠሙ በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እያሳደረ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይገልጻል።

የለአም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪን ያቀረበው መንገስት በበኩሉ ድርቁ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአራቱ ክልሎች በበልግ ወቅት መጣል የነበረበት ዝናብ በበቂ ሁኔታ ባለመጣሉ ምክንያት ድርቁ የተከሰተ ሲሆን፣ አብዛኛው አካባቢ ባለፈው አመት በተመሳሳይ ችግር ውስጥ መቆየቱ ድርቁ የከፋ እንዲሆነ አስተዋጽዖ ማደረጉን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ2005-2009 አም ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ወደ 378 ሺ ህጻናት ሞት ተከስቶ እንደነበር የተባበሩት መንግስታት አንድ አለም ቀፍ ጥናት ዋቢ በማድረግ አስታወቀ።

Cost of Hunger in Africa በሚል ፕሮጄክት የተካሄደው ይኸው ጥናት ከ12 ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑት የሃገሪቱ ህጻናት መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት እድገታቸው ሊስተጓጎል መቻሉን አመልክቷል።

በሃገሪቱ በተደጋጋሚ በድርቅ አደጋ የመመታት ዕጣ ቢኖራትም፣ የሚደርሱ ጉዳቶች ግን በአግባቡ ሊታወቅ አለመቻላቸውን ተመድ ጥናቱን ዋቢ በማድረግ በኢትዮጵያ የድርቅ ሁኔታ ላይ ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል።

ይኸው ከ300 ሺ በላይ ለሆኑ ህጻናት ሞት ምክንያት የነበረው የድርቅ አደጋ ለሃገሪቱ ፈታኝ ወቅት ሆኖ ማለፉንና 16 በመቶ አካባቢ የሚሆነውን የኢትዮጵያ አጠቃላይ አመታዊ ምርት ዋጋ አስከፍሎ እንደነበርም ተመልክቷል።

በአፍሪካ ካሉ ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ ለተደጋጋሚ የድርቅ አደጋ በመጋለጥ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እየደረሱባት ሲሆን፣ ለሁለት ተከታታይ አመታት የተከሰተው የድርቅ አደጋ ዘርፉ ብዙ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተተንብዮአል።

በተለይ በድርቁ ምክንያት ከፍተኛ የምግብ እትረት የሚደርስባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት የአካል እንዲሁም ዘላቂ የጤና ዕክል እንደሚደርስባቸው በጥናቱ ተመልክቷል።