የድርቅ አደጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በርካታ የቤት እንስሳት በመሞት ላይ መሆናቸው ተገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 7 ፥2009)

በኦሮሚያ ክልል አዲስ የድርቅ አደጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በርካታ የቤት እንስሳት በመሞት ላይ መሆናቸው ተገለጸ።

የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር በበኩሉ ችግሩን ለመቅረፍ ከሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች ወደ አካባቢው የመኖና የውሃ አቅርቦት እየተጓጓዘ መሆኑን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ማስተባበሪያ መምሪያና አለም-አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋማት አዲስ የተከሰተው ይኸው የድርቅ አደጋ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት እንዲሞቱ ማድረጉን በመግለጽ ላይ ናቸው።

በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ደቡብ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ውስጥ የተከሰተው የድርቅ አደጋ በአሁኑ ወቅት በእንስሶች ላይ ጉዳት ቢያደርስም በጥቂት ወራቶች ውስጥ ችግሩ በስፍራው ለሚኖሩ ሰዎች ስጋት እንደሚሆን ተመልክቷል።

አለም አቀፍ የእርዳታ ጥሪ ለዚሁ የድርቅ አደጋ ያቀረበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በተያዘው አመት የምግብ ድጋፍ የሚሹ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።

ባለፈው አመት በስድስት ክልሎች የተከሰተው ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ ሙሉ ለሙሉ ዕልባት ሳያገኝ አዲስ የድርቅ አደጋ መከሰቱ ለሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩም ተነግሯል።

በዚሁ አደጋ ጉዳት ይደርስባቸዋል ተብለው ከተገመቱ ስድስት ሚሊዮን ሰዎች መካከል ከ300ሺ የሚበልጡ ህጻናት በምግብ እጥረት ምክንያት የአካልና የጤና ችግር ይደርስባቸዋል ተብሎ ስጋት መኖሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይገልጻል።

ከአንድ አመት በፊት በስድስት ክልሎች ተከስቶ ለነበረው የድርቅ አደጋ የመንግስት ባለስልጣናት በወቅቱ አለም አቀፍ ድጋፍ ባለማድረጋቸው ከተለያዩ አካላት ወቀሳ ሲቀርብባቸው እንደነበር ይታወሳል።

የተባበሩት መንግስታት አዲስ ለተከሰተው የድርቅ አደጋ አለም አቀፍ የእርዳታ ጥሪ ቢያቀርብም የኢትዮጵያ መንግስት ግን ያቀረበው ነገር እንደሌለ ታውቋል። ይሁንና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን አደጋው “ከእጃችን ሳይወጣ በቁጥጥር ስር ይውላል” ሲሉ በቅርቡ ለሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች መናገራቸው ይታወሳል።