የድርቅ አደጋው እስከ ነሃሴ 2008 ሊቀጥል እንደሚችል ተመድ አስታወቀ

ኢሳት (ጥቅምት 10 ፡ 2008)

በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ እስከተያዘው አመት ማጠናቀቂያ ነሀሴ ወር ድረስ ቀጣይ ሊሆን እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዛሬ ማክሰኞ አሳሰበ ።

በሀገሪቱ ተከስቶ ያለው የምግብ እርዳታ ፍላጎትም ከአራት አመት በፊት በአፍሪካ ቀንድ ተከስቶ ከነበረው አጠቃላይ መጠን ጋር ሲነጻጸር ከፍ ብሎ መገኘቱን ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

በጉዳዩ ዙሪያ ከለጋሽ ሀገራት የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ በበኩላቸው የድርቁ አደጋ ትርፍ አምራች የሆኑትን አካባቢ ጉዳት አያደርስም ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ከሀገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ማክሰኞ ወቅታዊ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የድርቁ አደጋ ተባብሶ በመቀጠል እስከ ነሀሴ ወር ድረስ ተዛማች ሊሆን እንደሚችል ገልጿል ።

የድርቁ አደጋ በአሁኑ ሰአት በስድስት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ በርካታ ዞኖች ከፍተኛ ጉዳትን እያደረሰ እንደሚገኝ ያስታውቀው ድርጀቱ በአንዳንድ አካባቢዎች 80 በመቶ የሚሆን ምርታማነትን እንደሚቀንስ አመልክቷል።

በቅርቡ በተደረገው ጥናትም እድሜያቸው ከስምስት አመት በታች ሆኖ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ህጻናት ቁጥር በ 32.5 በመቶ ማደጉ ታውቋል።

በኢትዮጵያ ያለው የበጋ ወቅት እየተጥናከረ መሄዱን ተከትሎም የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ፈላጊዎች ቁጥር 15 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድጋሚ የገለጸ ሲሆን በተያዘው አመት በሀገሪቱ ተከስቶ ያለውን የድርቅ አደጋም በ30 አመት የከፋ ሊሆን እንደሚችልአሳስቧል።

መንግስት በበኩሉ ከስምንት ሚሊዮን በላይ የደረሰው የተረጂዎች ቁጥር ወደ 10 ሚሊዮን ይደርሳል ሲል ትንበያን አስቀምጧል።

ዛሬ ማክሰኞ ከለጋሽ አገራትጋር በተለያዩ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክርን ያደረጉት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የድርቁ አደጋ ጉዳትን አያስከትልም ሲሉ መናገራቸውን ለመረዳት ተችሏል።

በሃገሪቱ ያይለውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ በርካታ ነዋሪዎች ቅያቸአውን ኣየለቀቁ እንደሚገኝ ትላንት ሰኞ ኒው ዮርክ ታይምስ መዘገቡ ይታወሳል።