የድርቁ ሁኔታ በእጅጉ እንዳሳሰበው ተመድ ገለጸ

ጥቅምት ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ መጽሄት ይዞት በወጣ ዘገባ፣ ከ80 እስከ 85 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን የቆዳ ስፋት የሸፈነው የዝናብ መዛባት፣ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል ብሎአል።
ሁኔታዎች እየባሱ ቢሄዱም ፣ በመንግስት በኩል የቀረበው የእርዳታ ጥሪ በቂ መልስ አላገኘም የሚለው መጽሄቱ፣ ከጥር በሁዋላ ያለውን የምግብ አቅርቦት ለመሸፈን አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፍልግ ገልጿል። መንግስት ለገባያ ማረጋጋያ በሚል የገዛውን እህል እያከፋፈለ ነው። ይሁን እንጅ ጊዜው እየገፋ ሲመጣ ችግሩም እየተባባሰ እንደሚሄድ አስጠንቅቋል። በተለይ በተለይ ለሚቀጥሉት 8 ወራት ሁኔታዎች አስከፊ ሊሆኑ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
በተለይ በአማራ ክልል በምግብ የተጎዱ ህጻናት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የገለጸው ድርጅቱ፣ በዚሁ ክልል ከምግብ እጥረት ጋር በተያአዘ የእከክ በሽታ እየተስፋፋ መምጣቱንም ገልጿል። በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ወሎ፣ በምስራቅ ጎጃምና በዋግ ህምራ ዞኖች በሚገኙ 20 ወራደዎች በሽታው መስፋፋቱን መጽሄቱ ዘግቧል።