የድምጻችን ይሰማ ዋና መሪዎች እንዲከላከሉ ተበየነባቸው

(ሦስት)ቀን ፳፻፮ /  ኢሳት ዜና :- በሽብር ወንጀል ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት የድምጻችን ይሰማ መሪዎች ተከላከሉ መባላቸውን ጠበቃ  ተማም አባ ቡልጉ ተናግረዋል። 12 ሰዎች በነጻ የተለቀቁ ሲሆን፣ እነ አቶ አቡበከር አህመድና ሌሎች ደግሞ በተከሰሱበት ሽብር የማድረግ ወንጀል ሳይሆን ሽብር በማነሳሳት ጉዳይ ላይ እንዲካለከሉ ተበይኖአል። ሙራድ ሹኩር ጀማል፣  ኑሩ ቱርኪ  ኑሩ፣ ሼህ ባህሩ ኡመር ሸኩር እና ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸው ደግሞ ሽብርን በመርዳት በሚለው አንቀጽ ሰባት እንዲካለከሉ መበየኑን ጠበቃው ተናግረዋል። ተከሳሾች መከላከያቸውን  ከጥር 22 እስከ 27 እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ አዟል።

ውሳኔውን በተመለከተ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው ጠበቃ ተማም፣ ምንም እንኳ ተከላከሉ የተባሉት አንቀጽ የቅጣት መጠኑን ቢቀንሰውም፣  ግለሰቦቹ በነጻ መለቀቅ አለባቸው ብለው  እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ መንግስት የሽብር ጥቃት ተፈጽሟል በማለት በአንቀጽ 3 ያቀረበው ክስ ማስረጃ መጥፋቱንም አክለው ገልጸዋል( 08፡46-10፡17)

ብይኑ ሲሰጥ በእስረኞች በኩል ምንም አይነት የመደናገጥ ወይም የመረበሽ ምልክት አለማየታቸውን የተናገሩት ጠበቃው፣ የእኛ ደንበኞች ለምን እንደታሰሩ የሚያውቁ የሀይማኖት መምህራን እና ለእኛ ጽናትን የሚያስተምሩ ናቸው  ብለዋል(10፡25-10፡54 )

አቡበከር አህመድ፣   አህመዲን ጀበል መሃመድ ፣ ያሲን ኑሩ ኢሳአሊ ፣ ከሚል ሸምሱ ሲራጅ ፣ በድሩ ሁሴን ኑር ሁሴን ፣ ሼህ መከተ ሙሄ መኮንን ፣ ሳቢር ይርጉ ማንደፍሮ ፤ መሃመድ አባተ ተሰማ ፣ አህመድ ሙስጠፋ ሃቢብ ፣ አቡበከር አለሙ ሙሄ ፣ ሙኒር ሁሴን ሃሰን ፣ ሼህ ስኢድ አሊ ጁሃር ፣ ሙባረክ አደም ጌቱ አሊዬ እና ካሊድ ኢብራሂም ባልቻን የተመሰረተባቸውን ክስ ተከላከሉ ተብሎባቸዋል።

ችሎቱ ሃሰን አሊ ሹራባ ፣ ሼህ ሱልጣን ሃጂ አማን ፣ ሼህ ጀማል ያሲን ራጁኡ ፣ ሼህ ጣሂር አብዱልቃድር ፣ ሃሰን አቢ ሰኢድ ፣ አሊ መኪ በድሩ ፣

ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱሃፊ ፣ ሼህ አብዱራህማን ኡስማን ከሊል ፣ ወይዘሮ ሃቢባ መሃመድ ፣ ዶክተር ከማል ሃጂ ገለቱ እና ሁለቱ ድርጅቶች በነጻ ተሰናብተዋል።