ሐምሌ ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ባለፈው አርብ 70 የሚሆኑ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ፍርድ ቤት ቀርበው 28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል። በዛሬው እለት ደግሞ 8 የአመራር አባላት አራዳ ምድብ ችሎት ቢቀርቡም ወዲያውኑ ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተደርጓል።
የመንግስት ታጣቂ ሀይሎች ድምጻችን ይሰማ በማለት ጥያቄ ባቀረቡ ሙስሊሞች ላይ የጅምላ እስር እና ድብደባዎችን ፈጽመዋል። ትናንት እሁድና ዛሬ ሰኞ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ብቻ በአንዋር መስጊድ አካባቢ ሲዞሩ የታዩ ሲሆን፣ የፌደራል ፖሊስ ልዩ ግብረሀይል ፣ ጊዚያዊ ጣቢያ ብለው ባቋቋሙት ኡመር ሰመተር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በሜጋ አምፊ ቲያትር እና በአዲስ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ሰፍረው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሎአል።
በትናንትናው እለትም የፖሊስ አባላት በየሰፈሩ በመግባትና መታወቂያዎችን በማየት በርካታ ወጣቶችን እያሰሩ ወስደዋል።
ቅዳሜ ሐምሌ 14 ቀን 2004 ዓ.ም ከመርካቶ አንዋር መስኪድ፣ ከፒያሳ በኒ /ኑር/ መስኪድ፣ ከአዲሱ ሚካኤል አቅራቢያ፣ ከኳስ ሜዳ እና አብነት አካባቢ መስኪዶች በፌዴራል ፖሊስ የታፈሱ ሙስሊሞችና የተወሰኑ ክርስቲያኖች በምሽት በፖሊስ ኦራልና አቡቶቡስ የጭነት ካሚዮን ወደ ሠንዳፋ ፖሊስ ማሰልጠኛ ጣቢያ መወሰዳቸው ይታወቃል፡፡
ዜጎች በጊዜያዊነት በታሰሩበት አዲስ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ የወረዳ ጽ/ቤትና ደጃች ዑመር ሠመተር የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት እሥረኞች በነበሩበት ጊዜ በቪዲዮ መቀረፃቸውን ከምንጮቻችን አረጋግጠናል፡፡
ከአዲስ አበባ ፖሊስ የዜና ምንጮቻችን እንደተገለጸልን የተጓዥ ታሳሪዎች ቁጥር ከ አንድ ሺ የማያንስ ሲሆን በትናንትናው ዕለት የተወሰኑ የታሳሪያን ቤተሰቦች ሊጠይቋቸው ሠንዳፋ ድረስ ቢሄዱም ከቤተሰብ ጋር እንዲገናኙ ከበላይ አካል አልተፈቀደም ተብለው ብዙዎቹ ወደ አዲስ አበባና አቅራቢያ ከተሞች ተመልሰዋል፡፡
ትግርኛ ተናጋሪ የፌዴራል ፖሊስ ልዩ ግብረ ኃይል ከታሳሪዎች ሁሉ ያገኙትን የሞባይል ሥልክ ቀፎ፣ አይፖድ፣ ሰዓት እየነጠቁ በስልኩ የተነሱ ፎቶዎችን በመመልከት ሁኔታውን በፎቶ ቀርጸሃል በሚል በመወንጀልና በማስፈራራት ንብረቶቹን ሳይመዘግቡ ወደ ራሳቸው ኪስ ሲያስገቡ የተመለከቱ የዓይን እማኞች ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ሥፍራ በቡና ቤቶች የነበሩ ዜጎች ሁሉ እንዲወጡና እንዲፈተሹ በማድረግና መታወቂያ ካርዳቸውን በመመልከት የመኖሪያ አድራሻቸው ከአካባቢው ራቅ ያለ ዜጎችን ለምን እዚህ መጣህ በማለት በዱላ የደበደቧቸው ሲሆን፣ አንዳንዶችም እኔ ክርስቲያን ነኝ እያሉ የአንገታቸውን መስቀል እና የእምነት ማህተም /ክር/ ቢያመላክቱም የኢህአዴግ ልዩ ፖሊሶች በዱላ ከመደብደብ አልታቀቡም በማለት ተጎጂዎች ገልጸውልናል፡፡
ድምጻችን ይሰማ በሚሉ ሙስሊሞች እና በመንግስት መካከል ያለው ግጭት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ። መንግስት የመርካቶ አካባቢ ሰላም የሰፈነበት መሆኑን ለማሳየት የራሱን ካድሬዎች አቅርቦ ማናገሩን ዘጋቢያችን ገልጧል። ሙስሊሙ ገዢው ፓርቲ በፈጸመው ድርጊት ቂም መያዙንም፣ ትግሉንም እንደማያቆም ዘጋቢያችን የአነጋገራቸው ወጣቶች ገልጠዋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide