መጋቢት ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከትጥቅ ትግሉ ጊዜ አንስተው የህዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ(ህወሀት) ድምፅ የሆነው የድምጸ-ወያነ ራዲዮ አዘጋጆች የነበሩት ጋዜጠኛ ስልጣኑ ህሽ እና ጋዜጠኛ አንዶም ገብረሥላሴ የ አረና ለትግራይ ፓርቲ አባል ሆነው ተገኙ።
በዚህም ምክንያት ከሀያ ዓመታት በላይ ከሠሩበት ድምጸ ወያነ ራዲዮ ጣቢያ መባረራቸውን ፓርቲያቸው አረና ለትግራይ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
የፓርቲውን መግለጫ በመጥቀስ ሳምንታዊው ሰንደቅ እንደዘገበው፤ ከሁለቱ ጋዜጠኞች በተጨማሪም በሌሎች የአረና አባላት ላይ ከሥራ ገበታ መባረርን ጨምሮ እስከ አካላዊ ጥቃት የሚደርስ በደል እየተፈጸመባቸው ይገኛል።
ወጣት አያሌው፣ወጣት አምሃ ዶሪ፣አቶ ተሾመ ገብረመድህን፣ መምህር ይልማ ይኹኖ እና ኢንጂነር አብዱልውሀብ ቡሽራ በተባሉት አምስት የፓርቲው አባላት ላይ አካላዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ያመለከተው አረና፤ በ አቶ አስገደ ገብረሥላሴ፣ጥቃት በተፈፀመባቸው በአቶ ተሾመ ገብረመድህን፣በቄስ ጉዕሽ አረጋይ፣በ አቶ አማረ ተወልደ እና በ አቶ ዜናዊ አስመላሽ ላይ ደግሞ ክስ መመስረቱንና እስራት መፈፀሙን አመልክቷል።
እንደ አረና መግለጫ፤ጉዕሽ ገብረፃድቅ የተባሉ መምህርን ጨምሮ የድምፀ-ወያነ ራዲዮ አዘጋጅ በነበሩት ሁለቱ ጋዜጠኞች ላይ ደግሞ ከ ሥራ የማባረር እርምጃ ነው የተወሰደው።
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የኦሮምኛ ፕሮግራም ውስጥ በአዘጋጅነት ሢሰሩ የነበሩት እነ ዳበሳ ዋቅጅራ “የሌላ ፓርቲ አባል ናችሁ” ተብለው፦ “ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ለመናድ ማሴር” የሚል ክስ ተመስርቶባቸው ለዓመታት ታስረው መለቀቃቸው ይታወሳል።
አረና መግለጫውን ሲቋጭም ሁሉን አቀፍ ወከባና እንግልት በሁሉም የፓርቲው አባላት ላይ እየተፈፀመ መሆኑን ጠቁሟል።
በተለይ የመንግስት አካላትና የደህንነት ሰዎች በቤተሰብ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እየገቡ ሁከት በመፍጠር፣የኢኮኖሚ ዋስትና በማሳጣትና ትዳር በማፍረስ ጭምር በአባሎቹ ላይ ጫና እያሳደሩ መሆናቸውን ከፓርቲው መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide