(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 19/2010)
የደቡብ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ደኢሕዴን/ማዕከላዊ ኮሚቴ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ምትክ አቶ ሲራጅ ፈጌሳን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ።
የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት ሆነው እየሰሩ ያሉትን አቶ ደሴ ዳልኬን ደግሞ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ ሾሟል።
የደኢሕዴን ምርጫ ከዚህ ቀደም ይፋ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ባልታወቀ ምክንያት ዜናው እንዲነሳ ተደርጎ ማስተባበያ ተሰጥቶበት እንደነበር ይታወሳል።
የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ላለፉት 21 ቀናት ግምገማ ሲያካሂድ ቆይቶ አቶ ሲራጅ ፈጌሳን የድርጅቱ ሊቀመንበር በማድረግ መርጧል።የመከላከያ ሚኒስትር እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወታደራዊ እዝ ጸሃፊ የሆኑት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የፓርላማ ተመራጭም ናቸው።
እናም ደኢሕዴን አቶ ሲራጅ ፈጌሳን በሊቀመንበርነት መምረጡ በቀጣዩ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እጩ ተደርገው ሊሰየሙ የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል።እስካሁን ባለው ሂደት ኦሕዴድ ዶክተር አብይ አህመድን፣ብአዴን አቶ ደመቀ መኮንንን፣ደኢሕዴን አቶ ሲራጅ ፈጌሳን፣ሕወሃት በበኩሉ ዶክተር ደብረጺዮንን የየድርጅቶቹ ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል። በቀጣይነትም ሐገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት በሕወሃት አገዛዝ ዘመን የሚመሩት ከአራቱ አንዱ ይሆናሉ ማለቱ ነው።
ሕወሃት ዶክተር ደብረጺዮን ክልሉን እንዲመሩ አድርጎ በመሾሙ እጩ ሆነው እንደማይቀርቡ ከወዲሁ ሲገለጽ ስለነበር ለጠቅላይ ሚኒስትርነት በእጩነት ሊቀርቡ የሚችሉት ቀሪዎቹ ሶስት እንደሚሆኑ ታውቋል።የፖለቲካ ምሁራን እንደሚሉት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ከሌሎች ይልቅ በሕወሃት በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ የሚመረጡ ሰው ሊሆኑ ይችላሉ።ምክንያታቸው ደግሞ ከሕወሃት ጄኔራሎች ጋር በቅርበት የሚሰሩና ለአገዛዙ በመታዘዝ በኩል ይበልጥ የተመቹ ሰው ናቸው በሚል ነው።ያም ተባለ ይህ ግን ቀጣዩን የጠቅላይ ሚኒስትር ቦታ የሚይዘው የኢሕአዴግ ምክርቤት የድርጅቱን ሊቀመንበር በሚቀጥለው ረቡዕ ሲመርጥ ብቻ ይሆናል።የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አቶ ሲራጅ ፈጌሳን የድርጅቱ ሊቀመንበር ከማድረጉ ሌላ የክልሉ ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ ደሴ ዳልኬን ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ ሾሟል።የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ከነገበስቲያ ረቡዕ ይካሄዳል ተብሏል።የፓርላማው አስቸኳይ ስብሰባ ደግሞ አርብ እንደሚካሄድ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።