ታኅሣሥ ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የደኢህዲን/ኢህአዴግ ከፍተኛ ካድሬና የዞኑ ም/አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ሥጦታው ጋርሾ ከገዢው ፓርቲና መንግስት ጋር የፈጠሩትን ቅራኔ ተከትሎ በትውልድ አካባቢያቸው በና-ጸማይ ወረዳ ውስጥ ወጣቶችን አስከትለው መሸፈታቸውን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።
አቶ ሥጦታው ጋርሾ ከዞኑ የደህንነት ቢሮና አስተዳደር ጋር በተፈጠረ ቅራኔ ‹ተገምግመው › በተለያዩ የሙስ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸው ወደ ወህኒ ወርደው ከተፈቱ በኋላ ወደ ትውልድ ወረዳቸው በመሄድ በመንግስት ላይ ተቃውሞ ያላቸውን ወጣቶች በማሰባሰብ ጫካ መግባታቸውን ገልጸዋል።
የመንግስት ታጣቂዎች ወደ ወረዳው ሄደው ተደጋጋሚ አሰሳ ቢያደርጉም እስካሁን ሊይዙዋቸው አልቻሉም፡፡የአገር ሽማግሌዎችን በመያዝ በእርቅ ሥም አግባብተው ለመያዝ ወይም ግለሰቡ ያሉበትን ቦታ እንዲጠቁሙ የተደረገው ሙከራ እስካሁን ሊሳካ ያለመቻሉንና በዚህም ወረዳው ውስጥ ውጥረት መንገሱ ታውቋል ፡፡
የሃመርና የበና-ጸማይ ወጣቶች በወረዳው የአልዱባ ቀበሌን ፖሊስ ጣቢያ ማፈራረሳቸውና በተመሳሳይ ቀን ከአልዱባ ቀበሌ አልፎ በሚገኘው የበና-ጸማይና ሃመር ወረዳዎች ድንበር ላይ በቱሪስት መኪና ላይ ተኩስ መከፈቱን እንዲሁም በማጎ ካምፕ ድንበር ወደ ኩራዝ 2 ስኳር ፕሮጀክት መታጠፊያ ላይ የሳላማጎ ወረዳ ፖሊሶች ላይ ጥቃት ተፈጽሞ አንድ መሞቱና ሶስት መቁሰላቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡ አቶ ሥጦታውን ተክተው የዞኑን ም/አስተዳዳሪ የሆኑት የሃመር ተወላጁ አቶ አወቄ አይኬ ‹በቃኝ› ብለው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው ከዚህ ጉዳይ ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል በማለት በሃመር ወረዳ በሰፊው እየተነገረ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ረቡዕ በሃመር ወረዳ ዲመካ ከተማ አንድ የ7 ልጆች እናት የተገደሉ ሲሆን፣ ህዝቡ ዛሬ ወደ አደባባይ ወጥቶ ድርጊቱን አውግዟል። ውጥረቱ አሁንም እንዳለ ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል
በሌላ በኩል ታህሳስ 17 ቀን 2009 ዓ.ም ከሃመር ወረዳ ከብቶች መዘረፋቸውን ተከትሎ ከሃመር ወረዳ ወደ ኩራዝ 4 ስኳር ፕሮጀክት የሚገኝበት ኛንጋቶም ወረዳ የሚወስደው መንገድ መዘጋቱን፣ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ ዛሬ ጠዋት መከፈቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።