ኢሳት (ግንቦት 21: 2009)
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ እገታ የተፈጸመበትን አንድ ኢትዮጵያዊ ነጋዴ ከእገታ ማስለቀቁን ሰኞ አስታወቀ። ስሙ ይፋ ባልተደረገው ኢትዮጵያዊ ነጋዴ ላይ እገታውን ፈጽመዋል የተባሉ ሶስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ኒውስ 24 የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።
ሶስቱ ግለሰቦች ኢትዮጵያዊ ነጋዴውን ከጆሃንስበርግ ከተማ በቅርቡ ርቀት ላይ ከሚገኘው የኦ አር ታምቦ (O R Tambo) አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የንግድ ስምምነት እንፈጽማለን ብለው አታለው እንደወሰዱት ተመልክቷል።
ራሳቸውን ነጋዴ መስለው የቀረቡት ሶስቱ ተጠርጣሪዎች ኢትዮጵያዊውን ነጋዴ ከአየር ማረፊያ ከወሰዱት በኋላ በአንድ መኖሪያ ቤት እጅና አይኑን አስረው እንዳቆዩት ካፒቴን ሎንጌሉ ድላሚኒ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
ተጣርጣሪዎች ከግለሰቡ የክሬዲት ካርዶችን በመቀበል 25 ሺ ራንድ (2ሺ ዶላር) የሚያውወጣ ልብስና ጌጣጌጥ ግዥን እንደፈጸሙት የፖሊስ ሃላፊው አስረድተዋል። ከእጅ ሽጉጣቸው ጋር በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ሶስቱ ግለሰቦች በእገታ የያዙትን ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች በስልክ በመገናኘት የገንዘብ ጥያቄን እንዳቀረቡም ፖሊስ አክሎ አመልክቷል።
ይሁንና የታጋቹ ቤተሰቦች ጉዳዩን በአስቸኳይ ለፖሊስ በማሳወቃቸው ምክንያት የጸጥታ አባላት እገታው በተፈጸመበት ቤት በመገኘት ኢትዮጵያዊውን ነጋዴ መታደግ እንደቻሉ ጋዜጣው በዘገባው አስፍርረዋል።
ታጋቹ ነጋዴ በተጠርጣሪዎቹ እጅ ስር እያለ እንግልት የደረሰበ ሲሆን፣ ግለሰቦቹ የጦር መሳሪያን በመያዝ ማገትና ማጭበርበርን በመፈጸም የሚል ክስ እንደሚመሰረትባቸው የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አስታውቋል።
ሶስቱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር በዋሉ ጊዜ ወንጀሉን ለመፈጸም የተከራዩት ተሽከርካሪና ህጋዊ የሆነ የጦር መሳሪያ መያዙም ታውቋል።
ፖሊስ አክሎም ከግለሰቦች ጋር የንግድ ግንኙነትና ስምምነት ለመፈጸም በሚል እንዲህ ያለ እንቅስቃሴን የሚያደርጉ ግለሰቦችና አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስቧል።