የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ ከስልጣናቸው እንዲነሱ ተጠየቁ

ኢሳት (ኅዳር 19 ፥ 2009)

የሙስና ክስ እየቀረበባቸው የሚገኙት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ ከስልጣናቸው እንዲነሱ ሶስት የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸው ጠየቁ።

የሃገሪቱ ገዢው የአፍሪካ ብሄራዊ ምክር ቤት እያካሄደ ባለው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የታደሙት ሶስቱ ሚኒስትሮች ዙማ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን እንዲለቁ በይፋ መጠየቃቸውን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የሃገሪቱ የጤና ጥበቃ፣ ቱሪዝምና የስራ ሚኒስሮች ለፕሬዚደንቱ ጥያቄን ያቀረቡ ሶስቱ ሚኒስትሮች ሲሆኑ፣ ጃኮብ ዙማ በስልጣን ለመቆየት እየቀረበባቸው ያለን ክስና ቅሬታ ለማስተባበል እየሞከሩ መሆኑ ተነግሯል።

የአፍሪካ ብሄራዊ ምክር ቤት ለስልጣን ከበቃ ከ20 አመት በኋላ ከመቼውም ጊዜ በላይ በበርካታ የሃገሪቱ ዜጎች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እየቀረበበት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።

ይህንን የዙማ የካቢኔ ሚኒስትሮች ፕሬዚደንቱ ስልጣንት እንዲለቁ ጥያቄን ሲያቀርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።

ይሁንና የገዢው ፓርቲ አባላትና አመራሮች በጃኮብ ዙማ ሁኔታ ለሁለት በመከፈላቸው ምክንያት ዙማ በቅርቡ ስልጣን ይለቃሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ የሃገሪቱ የፖለቲካ ተንታኞች አስረድተዋል።

ባለፈው አመት ፕሬዚደንት ዙማ ከመንግስት ካዝና ወደ 20 ሚሊዮን ዶላር አካባቢን በመውሰድ የግል መኖሪያ ቤታቸውን ለማደስ ተጠቅመዋል በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው የሃገሪቱ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንቱ የወሰዱትን ገንዘብ እንዲመልሱ ውሳኔን አስተላልፎ የነበረ ሲሆን፣ ድርጊቱ ጃኮብ ዙማ ያላቸውን ተቀባይነት እንዲያጡ ማድረጉም ይነገራል።

በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን በስልጣን ላይ ያለው የዙማ መንግስት ድህነትን ለመቅረፍና ሙስናን ለመዋጋት የወሰደውምንም  እርምጃ የለም በሚል የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የሃገሪቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በበኩላቸው መንግስት በዩኒቨርስቲ ትምህርት ላይ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ ያየዘውን እቅድ በመቃወም በተደጋጋሚ አደባባይ በመውጣት በመንግስት ላይ ተቃውሞን ሲያቀርቡ መሰንበታቸውም ይታወሳል።

የተማሪዎች ጥያቄና ወደ ግጭት መቀየር መጀመሩ ተከትሎ የደቡብ አፍሪካ መንግስት የዋጋ ጭማሪውን ለተወሰነ ጊዜ እንዲዘገይ ያደረገ ሲሆን፣ በሃገሪቱ እየተባባሰ የመጣውን ህዝባዊ ተቃውሞ በ20 አመት ታሪክ ውስጥ የከፋው እንደሆነ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።