የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ያለውን ቢሮክራሲ ተቃወሙ

ኢሳት (ጥቅምት 14 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ የባንክ ዘፍን ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች በሃገሪቱ ተንሰራፍቶ ይገኛል ያሉትን የመንግስት ቢሮክራሲ ተቃወሙ።

የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ እድገቱን ለማገዝ በሚል የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ ጥረት ቢያደርግም በኢንቨስትመንት በሚሰማሩ አካላት ላይ እምነት የለውም ሲሉ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች ቅሬታ ማቅረባቸውን አፍሪካ ኒውስ ሰኞ ዘግቧል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ በሲሚንቶና በኮንስትራክሽን ኢንቨስትመንት ስራ ላይ ለመስራት ወደ ሃገሪቱ የገቡት ግሩፕ ፋይቭ (Group Five) እና PPC የተሰኙ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ጊዜ ጀምሮ በመንግስት ቢሮካራሲ እየተቸገሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር በደቡብ አፍሪካ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ኩባንያዎቹ የኢትዮጵያ መንግስት ቢሮክራሲን አሻሽላለሁ ሲል የገባው ቃል በወረቀት ላይ ብቻ መቅረቱን እንደገልጸ የዜና አውታሩ በዘገባው አመልክቷል።

የግሩፕ ፋይቭ (Group Five) ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት ቶኒ ሞቴ የኢትዮጵያ መንግስት በሚያስገርም ሁኔታ ለኢንቨስትመንት ስራዎች አስቸጋሪ ሆኖ ይገኛል ሲሉ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝትን አድርገው የነበሩት የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርከል በሃገሪቱ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሃብቶች በቢሮክራሲ ላይ ቅሬታን እያቀረቡ እንደሆነ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

መንግስት ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከትሎ ስታንዳርድ ባንክ የተሰኘው የደቡብ አፍሪካ ባንክን ጨምሮ የቱርክና የጀርመን እንዲሁም የኬንያ ባንኮች በብድር አቅርቦት ላይ ለመሰማራት ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ታውቋል።

ይሁንና ኩባንያዎቹ በመንግስት የተገባላቸው ቃል ተግባራዊ አለመደረጉንና ስራቸውን በአግባቡ እያካሄዱ እንዳልሆነ በመግለጽ ላይ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ለአንድ አመት ያህል ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየውና ከወራት በፊት በአማራ ክልል የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ በሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተገልጿል።

ህዝባዊ ተቃውሞ እያደረሰ ባለው በዚሁ ተፅዕኖ የሃገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በመስከረም ወር ላይ ማሻቀብን በማሳየት ወደ 7 በመቶ ማደጉን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ይፋ አድርጓል።

በምግብ ነክ ዋጋዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት የተመዘገበ ሲሆን፣ በነሃሴ ወር 4.4 በመቶ የነበረው የዋጋ ግሽበት በመስከረም ወር ከስድስት በመቶ ማሻቀቡን ኤጀንሲ በሪፕርቱ አስፍሯል።

በስጋ ወተትና በጥራጥሬ የምግብ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪው እያደገ መምጣቱን ያስታወሰው የስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እያሻቀበ ያለው የዋጋ ግሽበት ለኢኮኖሚ እድገቱ ስጋት መሆኑን አመልቷል።