ኢሳት (ታህሳስ 6 ፥ 2009)
የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳል ባኪር በስልጣን ዘመናቸው ለሰሯቸው ስህተቶች የሃገሪቱ ዜጎች ይቅርታን እንዲያደርጉላቸው ጠየቁ።
የይቅርታ ጥያቄያቸውን በፓርላማ ተገኝተው ያቀረቡት ፕሬዚደንቱ በደቡብ ሱዳን ሰላማዊ ድርድር እንዲካሄድ ጥሪን በማቅረብ ለሁሉም የተቃዋሚ ሃይሎች የደህንነት ዋስትና እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋል።
በሃገሪቱ ይካሄዳል የተባለውን ሁሉ አሳታፊ ድርድር በሃገር ውስጥና በውጭ ያሉ የተቃዋሚ ሃይሎች በአንድ በማሰባሰብ ለደቡብ ሱዳን ሰላም የሚያስፈልግ እንደሆነ ሳልባኪር አስታውቋል።
የቀድሞውን ምክትል ፕሬዚደንትና የአማጺ ቡድኑ መሪ የሆኑትን ሪክ ማቻር በስም ከመጥራት የተቆጠቡ ኪር በውጭ ሃገር ያሉ አመራሮችም ደህንነታቸው ተጠብቆ በሰላም ድርድሩ ተሳታፊ መሆን እንደሚገባቸው ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በመንግስትና በአማጺ ቡድኑ መካከል ከወራት በፊት በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰን ግጭት ተከትሎ ሪክ ማቻር ከህገሪቱ በመሰደድ ወደ ጎረቤት ሱዳን ከኮበለሉ በኋላ በደቡብ አፍሪካ እንደሚገኙ ሮይተርስ ሃሙስ ዘግቧል።
የአማጺ ቡድኑ መኮብለልን ተከትሎ በጉዳዩ ዙሪያ ምክክርን ያካሄዱት የደቡብ ሱዳን እና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አንደኛው የሌላውን ሃገር አማጺ ከመደገፍ እንዲቆጠቡ ስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።
ይህንኑ ስምምነት መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያ ሪክ-ማቻር ወደ ሃገሯ እንዳይገቡ እገዳን የጣለች ሲሆን፣ ባለፈው ወር በአዲስ አበባ በኩል ወደ ደቡብ ሱዳን የአማጺ ዋና መቀመጫ ፓጋግ ለመጓዝ እቅድ የነበራቸው ማቻር ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲመለሱ መደረጉ ይታወሳል።
በአዲሲቷ ሃገር ደቡብ ሱዳን በሁሉም አካላት ዘንድ ብሄራዊ ድርድር እንዲካሄድ ጥሪን ያቀረቡት ፕሬዚደንት ሳል-ባኪር ድርድሩ በሌላ ገለልተኛ አካል እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ይሁንና ፕሬዚደንቱ ብሄራዊ ድርድሩ በማን እንደሚካሄድ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ በክልልና በሃገር አቀፍ ደረጃ ሁሉን አሳታፊው ድርድር ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የሳል-ቫኪርን የይቅርታና የብሄራዊ ድርድር ጥሪ በተመለከተ የአማጺ ቡድኑ መሪ ሪክ ማቻር እስካሁን ድረስ ምላሽ ባይሰጡም ደቡብ አፍሪካ ሁለቱ ወገኖች ልዩነታቸውን እንዲያስወግዱ ጥረት እያደረገች መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።