የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ አመራሮች በጋምቤላ ግድያ ውዝግብ ውስጥ ገቡ

ኢሳት (ሚያዚያ 13 ፥ 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት በጋምቤላ ክልል በተፈጸመው ጥቃት የደቡብ ሱዳን መንግስትና አማጺያን እጃቸው የለበትም ቢልም የሃገሪቱ የፖለቲካ አመራሮች በጥቃቱ ዙሪያ ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ተገለጠ።

የሙርሴ ጎሳ ታጣቂዎች በብዛት የሚኖሩበት የደቡብ ክልል የቦማ ግዛት ገዥ የሆኑን ባባ መንዳ ጥቃቱ ኮብራ ተብሎ በሚጠራ አንጃ መፈጸሙን ይፋ እንዳደረጉ አሶሼይትድ ፕሬስ ሃሙስ ዘግቧል።

ይኸው ታጣቂ ሃይልም በሙርሴና በአኝዋክ የጎሳ ታጣቂዎች የሚመራ ሲሆን ቡድኑ ከሶስት አመት በፊት ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረሙንና በሃገሪቱ ብሄራዊ ጦር ውስጥ መካተቱን ሃላፊው አስታውቀዋል።

ይሁንና የኮብራ አማጺ ቡድን አመራር የሆኑት ዴቪድ ያኡ ያኡ ቡድኑ  በጋምቤላው ጥቃት እንደሌለበት አስተባብለዋል።

የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት በጥቃቱ እጁ ማን እንዳለበት እርስ በዕርስ መወነጃጀል ቢጀምሩም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የደቡብ ሱዳን መንግስትም ሆነ የአማጺ ቡድን ከጥቃቱ ጀርባ እጃቸው የለበትም ሲሉ በጥቃቱ ማግስት ማረጋገጫ መስጠታቸው ይታወሳል።

ይሁንና የደቡብ ሱዳን አመራሮች በዚሁ ጥቃት አዲስ ውዝግብ ውስጥ ገብተው እንደሚገኝ አሶሼይትድ ፕሬስ በዘገባው አስፍሯል