የደቡብ ሱዳን ነዋሪዎች ከኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ጋር አለመግባባት ላይ ናቸው ተባለ

ኢሳት (ግንቦት 5 ፥ 2008)

በቅርቡ ከጋምቤላ ክልል ታፍነው የተወሰዱ ህጻናትን ለማስለቀቅ በሚል ወደጎረቤት ደቡብ ሱዳን የገቡ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከነዋሪዎች ጋር አለመግባባት ውስት መሆናቸውን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አርብ ዘገቡ።

ከጋምቤላ ክልል በቅርቡ ርቀት ላይ ከሚገኘው የፓቻላ ግዛት የሚኖሩት ነዋሪዎች ወታደሮች በእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸው የጸጥታ ስጋትን አሳድረውባቸው እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

በፓቻላ አስተደደር አካባቢ ወሰጥ ሶስት ሺ የሚጠጉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሰፍረው እንደሚገኙ የተናገሩት ነዋሪዎች፣ ወታደሮቹ በሃይል የውሃ መገኛ ቦታዎች እየወሰዱባቸው መሆኑን እንዳስታወቁ ራዲዮ ታማዙጂ በዘገባው አቅርቧል። ከጋምቤላ ክልል በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ስፍራ ተሰማርተው የሚገኙት የኢትዮጵያ ወታደሮች በደቡብ ሱዳን መንግስት እና በሙሪሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድርድር የተለቀቁ ህጻናትን በቅርበት እየተቀበሉ እንደሆነ ታውቋል።

የደቡስ ሱዳን መንግስት የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደሃገሪቱ እንደገቡ ቢገልፅም፣ ወታደሮች ምንም አይነት እርምጃን እንዳይወስዱ መደረጉን በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የታፈኑ ህጻናትን ለማስለቀቅም የደቡብ ሱዳን ተወካዮች ከታጣቂዎች ጋር ድርድርን እያካሄዱ ሲሆን በድርድሩ ዙርያ ግን የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።

በፓቻላ አስተዳደር ሰፍረው የሚገኙት የኢትዮጵያ ወታደሮችም ታፍነው የተወሰዱት ህጻናት በድርድር ተለቀው እስከሚጠናቀቁ ድረስ በአካባቢው እንደሚቆዩ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

ይሁንና የወታደሮቹ ቆይታ ከነዋሪዎች ጋር አለመግባባትን የፈጠረ ሲሆን እስከ አርብ ድረስም 44 ህጻናት ወደ ጋምቤላ ክልል መግባታቸው ታውቋል።