(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 16/2010)
አርባ የሚሆኑ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት በጦር ወንጀለኝነትና በሰብአዊ መብት ጥሰት በግል ሊጠየቁ እንደሚችል አንድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት ይፋ አደረገ።
ቢቢሲ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ሪፖርት ጠቅሶ እንደዘገበው በደቡብ ሱዳን አስገድዶ መድፈር፣የአካል መጉደል፣ስቃይና እንግልት እንዲሁም ከመኖሪያ አካባቢ መፈናቀል በሰፊው ሲፈጸም ነበር ብሏል።
ሪፖርቱ እጅግ አሰቃቂ ነበር ካለው ድርጊት ውስጥ ሕጻናት እናቶቻቸው ሲደፈሩ እንዲመለከቱ ይደረግ ነበር፣ወንዶች ጭምር የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል ብሏል።
አንድ ከጥቃት ያመለጠች ነፍሰጡር እናት እንደተናገረችው ደግሞ የሱዳን ሕዝብ ነጻ አውጪ ሰራዊት ወታደሮች በማረኳቸው ተቃዋሚዎች ላይ ሰቆቃና የአካል ማጉደል ተግባር ሲፈጽሙ መመልከቷን ተናግራለች።
የአንድ ቤተሰብ አባል በሌላው ላይ ጥቃት እንዲፈጽም ይደረግ ነበር፣ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉም ፈጽመውታል ብሏል ሪፖርቱ።
በደቡብ ሱዳን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 የሰላም ስምምነት ቢፈረምም በመንግስት ውስጥ በተፈጸመው መከፋፈል እየተካሄደ ያለው ግጭት ለብዙዎች ሕይወት መጥፋትና ስቃይ ምክንያት ሆኗል።
ሪፖርቱ ለጊዜው በወንጀሉ ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን የባለስልጣናት ስም ባይጠቅስም ወደፊት ለፍርድ በሚቀርቡ ጊዜ ይፋ እንደሚሆን ጠቁሟል።