ኢሳት ( ግንቦት 1 ፥ 2008)
የደቡብ ሱዳን መንግስት በቅርቡ ከጋምቤላ ክልል ታፍነው የተወሰዱ ህጻናትን በድርድር ማስለቀቅ መጀመሩን ሰኞ ገለጠ።
ታፍነው የተወሰዱ ህጻናት ያሉበት ስፍራ መታወቁንና እየተካሄደ ባለው ድርድርም የተለቀቁ 19 ህጻናት ሰኞ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ መደረጉን የደቡብ ሱዳን ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ሌተናል ጄኔራል ዴቪድ ያው ያው አስታውቀዋል።
በቅርቡ በርካታ ታንኮችና ከባድ መሳሪያዎችን በመታጠቅ ወደ ደቡብ ሱዳን ዘልቆ ገብቷል የተባለው የኢትዮጵያ መከላከያ ስራዊትም ምንም እርምጃ ሳይወስድ፣ ሊወስድ ካሰበው ድርጊት መታቀቡን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት ከታጣቂ ሃይሎች ጋር ድርድርን እያካሄደ እንደሆነ ቢገልፅም፣ ከታጣቂ ወገኖች ስለቀረቡ ጥያቄዎች የሰጠው መረጃ የለም።
የሃገሪቱ ባለስልጣናት በቅርቡ ተጥለው የተገኙ 36 ህጻናት በአንድ መንደር መገኘታቸውንና ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ሰኞ በጋምቤላ ክልል ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ከተደረጉ ህጻናት በተጨማሪም 52 ህጻናትን በቅርቡ ኢትዮጵያ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ጥቃቱ በተፈጸመ ጊዜ ከታጣቂዎቹ መካከል 60 ዎቹ እንደተገደሉ መግለጹ ይታወሳል።
በክልሉ በተፈጸመው ጥቃት ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያን ተገድለው ከ20ሺ የሚበልጡት ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውም ይታወቃል። ጥቃቱን ፈጽመዋል የተባሉት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በትንሹ 125 ህጻናትን አፍነው መውሰዳቸውንም የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከ 208 በላይ ኢትዮጵያውያንን ገድለው ከ 100 የሚበልጡ ሀጻናትን ያገቱት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ባሳለፍነው ሳምንት ተጨማሪ ጥቃት ፈጽመው ኢትዮጵያውያን አግተው መውሰዳቸው ታውቋል። የአካባቢ ምንጮች ለኢሳት እንደገለጹት፣ የሙርሌ ታጣቂዎች አርብ ሌሊት ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው በመግባት ሕጻናትን አግተው ወስደዋል።
የአኝዋክ ሰርቫይቫል ቡድን ዳይሬክተር አቶ ኒካዋ ኦቻላ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጠዋል አራት ሕጻናት በሙርሌ ታጣቂዎች መወሰዳቸውን ለኢሳት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ታጋዮች ህጻናት እንደሚያስመልስ እየተናገረ ባሉበት ሰአት ተጨማሪ ሕጻናት ታግተው መወሰዳቸው አነጋጋሪ ሆኗል። ሆኖም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀደም ሲል ከታገቱት ሕጻናት 19 መመለሳቸውን የዘገበ ሲሆን ባለፈው አርብ በተጨማሪ ስለታገቱት አርት ህጻናት የገለጸው ነገር የለም።