ኢሳት (ጥር 8፥ 2009)
የደቡብ ሱዳን መንግስት በአባይ ወንዝ ዙሪያ ከግብፅ ጋር ተባብሮ ለመስራት ስምምነት መድረሱ ተገለጸ።
ሃገሪቱ ከግብፅ ጋር የደርሰችው ይኸው ስምምነት “ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ወዳጅነት አያበላሸውም ወይ?” ተብለው የተጠየቁ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ሃገራቸው ለኢትዮጵያ ስትል ጥቅሟን መስዋዕት አታደርግም ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል።
በቅርቡ በደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳል-ባኪር የተመራ የልዑካን ቡድን ወደ ግብፅ በማቅናት ከግብፅ ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ጋር በአባይ ግድብና በአጠቃላይ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ ስምምነት ማድረጋቸውን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ለሳል-ባኪር መንግስት ቅርብ የሆኑ ባለስልጣናት የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ሙሉ የመጠቀም መብት አስመልክቶ ሰፊ ውይይት ማካሄዳቸውንና ስምምነት መድረሳቸውን እንደገለጸ ኒያሚሌፒዲያ የተሰኘ ጋዜጣ አስነብቧል።
ይሁንና የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት በግብፅ ያደረጉት ጉብኝት ሃገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙንት ሊያሻክረው እንደሚችል የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች በመግለጽ ላይ ናቸው።
የሃገሪቱ ባለስልጣናት በበኩላቸው አዲሲቷ ሃገር ደቡብ ሱዳን ለኢትዮጵያ ስትል ጥቅሟን መስዋዕት እንደማታደርግ ከግብጽ ጋር የተደረሰው ስምምነት ጥቅምን ያስቀደመ እንደሆነ ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳንና የግብፅ መንግስታት የደረሱትን ይህንኑ ስምምነት “ቆሻሻው ስምምነት” በማለት የሚጠሩት የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው የሁለቱ ሃገራት አዲስ ትብብር ለኢትዮጵያ መንግስት ያልተጠበቀ እንደሚሆን አስታውቀዋል።
የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ለሀገሪቱ የአማጺ ቡድኖች የመሳሪያ ድጋፍን ያደርጋል ሲሉ ቅሬታን ማቅረባቸው ይታወሳል።
ይህንኑ ቅሬታ ተከትሎ ሁለቱ ሃገራት ከወራት በፊት አንደኛው ሃገር የሌላኛው ሃገር ተቃዋሚ ቡድንን ከመደገፍ እንዲቆጠብ የሚያደርግ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፣ ስምምነቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ የአማጺ ቡድኑ መሪ ሪክ-ማቻር ወደ ሃገሯ እንዳይገቡ እገዳን ጥላለች።
ይህ ባለበት ሁኔታ ደቡብ ሱዳን በአባይ ወንዝ ዙሪያ ከግብፅ ጋር ተባብሮ ለመስራት የደረሰችው ውሳኔ በኢትዮጵያና በሃገሪቱ መካከል ልዩነት መኖሩን የሚያሳይ እንደሆነ ተነግሯል።
የግብጽ መንግስት ከሌሎች ሃገራት በተሻለ መልኩ ለደቡብ ሱዳን ድጋፍ ለመስጠት በመዘጋጀቱ ጥቅማችንን በማስቀደም ስምምነት ደርሰናል ሲሉ አብርሃም ቾል የተባሉ የፕሬዚደንት ሳል-ባኪር መንግስት ባለስልጣን ለኒያሜሊፒድያ ፕሬስ ገልጸዋል።
በሁለቱ ሃገራት መካከል የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ ኢትዮጵያ ለወራት አስራ ያቆየቻቸውን ሶስት ግብጻውያን በመልቀቅ ከግብጽ ጋር ባለመግባባቶች ዙሪያ በቅርቡ ውይይት እንደሚካሄዱ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።