ኢሳት (ታህሳስ 24 ፥ 2009)
የደቡብ ሱዳን መንግስት በኢትዮጵያ በስደት ላይ የሚገኙ የሃገሪቱ ዜጎችን በሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ለማማከር የብሄራዊ የዕርቅ ልዑክ ወደ ጋምቤላ ክልል ለመላክ መወሰኑ ተገለጸ።
በሪክ-ማቻር የሚመራው አማጺ ቡድን በበኩሉ የፕሬዚደንት ሳልባኪር መንግስት በደቡብ ሱዳን ዕርቅ ላማምጣት ነው በሚል የወጠነው ሃሳብ የአፍሪካ ህብረትንና ሌሎች አለም አቀፍ አካላትን ለማታለል የተወሰደ ዕርምጃ ነው ሲል ድርጊቱን አጣጥሎታል።
የተለያዩ የህብረትሰብ ክፍል ተወካዮች ያካተተ ነው የተባለው ይኸው የደቡብ ሱዳን የልዑካን ቡድን በተያዘው ሳምንት መጨረሻ ላይ ወደ ጋምቤላ ክልል የሚያቀና ሲሆን ቡድኑ በአጠቃላይ የአንድ ወር ቆይታው እንደሚኖረው የደቡብ ሱዳን ዜና አገልግሎት ሰኞ ዘግቧል።
ይኸው የልዑካን ቡድን መቀመጫቸውን በጋምቤላ ክልል ካደረጉ ደቡብ ሱዳናዊያንና በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ የሃገሪቱ ዜጎችን በማግኘት ምክክሮችን ያካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
በአዲሲቷ ሃገር የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የሃገሪቱ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ተወስደው የሚገኙ ሲሆን፣ የተለያዩ አማጽያን የሚያስተባብሩ አካላትም በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ታውቋል።
ይሁንና ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በቅርቡ ባደረጉት ውይይት አንደኛው ሃገር የሌላኛውን ሃገር ተቃዋሚ አካል ላለመደገፍ ስምምነት የደረሱ ሲሆን፣ የስምምነቱ መድረስ በኢትዮጵያ የሚገኙ የደቡብ ሱዳን አማጺ አመራሮችን ህልውና አደጋ ውስጥ መክተቱ ተመልክቷል።
ይሁንና የፕሬዚደንት ሳልባኪር መንግስት ወደ ኢትዮጵያ በሚልከው የልዑካን ቡድን እነዚሁኑ አካላትን ለማግባባት ጥረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በቀድሞው የሃገሪቱ ምክትል ፕሬዚደንት ሪክ ማቻር የሚመራው የአማጺ ቡድን የሃገራቸው መንግስት በብቸኝነት ሰላም ለማምጣት በሚል የከፈተው ዘመቻ የአለም አቀፍ ማህበረሰበን ለማታለል የተወሰደ ዕርምጃ ነው ሲል ድርጊቱን ተቃውሞታል።
የአማጺ ቡድኑ አመራር የሆኑት ዴን ሞንግ የሳልባ-ኪር መንግስት በተናጠል በከፈተው በዚሁ ዘመቻ ሊያፍር ይገባዋል ሲሉ ለደቡብ ሱዳን ዜና አገልግሎት አስታውቀዋል።
የሃገሪቱ መንግስት ዕርቅ አመጣለሁ ብሎ የያዘውም ዕቅድ የአማጺ ቡድኑን ያሳተፈ ባለመሆኑም ውጤት እንደማያመጣ ሃላፊው አክለው ገልጸዋል። በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት አደራዳሪነት ሁለቱ ወገኖች ባለፈው አመት የጋራ የሽግግር መንግስት ለመመስረት ስምምነት ቢደርሱም ስምምነቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አለመግባባቱ ማምራቱ ይታወሳል።
በደቡብ ሱዳን መንግስት በአማጺ ቡድን መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ሪክ ማቻር በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ሲሆን፣ የደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናትና ሌሎች አካላት ሁለቱ ወገኖች ደግሞ ወደ ድርድር ለመመለስ ጥረት እያደረጉ መሆኑ ታውቋል።
ከአንድ አመት በላይ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ አድርገው የነበሩት ማቻር ከወራት በፊት ዳግም ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ እገዳ እንደተጣለባቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የሃገሪቱ አማጺ ቡድን አመራሮች ኢትዮጵያውያና ሌሎች አካላት ማቻርን ከሰላም ድርድር ለማውጣት ጥረት ያደርጋሉ ሲሉ ቅሬታን ያቀርባሉ።