በደሴ የሚገኙ መስኪዶች በፌደራል ፖሊስና በመከላከያ ሰራዊት እየተበረበሩ መሆኑ ታወቀ። እማኞች መስኪድ ሄዶ ሰግዶ መመለስ የማይታሰብና አሸማቃቂ ተግባር መሆኑንም ዘግበዋል።ምንጯቻችን ከደሴ እንደዘገቡት፤ ካለፈው አርብ ጀምሮ፤ ከ300 የሚልቁ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት እየተደበደቡ በየእስር ቤቱ ታጉረዋል።
ከደሴ ከተማ ከኢሳት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉ የደሴ ነዋሪዎች እንደገለጡት፤ የፌደራል ፖሊሶችና የመከላከያ ሰራዊት አባላት፤ ወደ መስጅድ ገብተው ብርበራ ከማድለጋቸውም በላይ፤ ብዙ በመስኪድ የተገኙ ሰዎች ተደብድበው ወደ እስር ቤት ተጉዘዋል።
ለደህንነቱ ሲል ስሙ እንዳይገለጥ የጠየቀው የደሴ ከተማ ነዋሪ፤ ኢማሙን እንፈልጋለን በሚል ሰበብ መስኪዶችን ደፍረው ብርበራ ያካሄዱት የፌደራል ፖሊሶች፤ በከተማዋ የደህንነት ምክትል ሀላፊ አቶ ሀብታሙ እየተመሩ መሆኑን አስረድቶታል።
በደህንነትና ፌዴራል ፖሊስ የሚደረገው ብርበራና ወከባ በመስኪድ ብቻ አላበቃም ያሉት የደሴ ነዋሪ፤ የኢማሙ ቤትም መበርበሩን ጨምርው ገልጠዋል።
በደሴ ከተማ የሚገኙ አምስት እስር ቤቶች ታፍሰው በታሰሩ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት ተሞልተዋል ያሉት የደሴ ከተማ ምንጮች፤ በየእስርቤቱ የታሰሩ ሰዎችን አሳዩን በሚል፤ የከተማዋ ነዋሪዎች የእስር ቤቶቹ አካባቢዎች ቢጨናነቁም ሰሚ እንዳልተገኘ፤ ይልቁንም በፌደራል ፖሊሶች ወከባና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጿል።