ጥቅምት ፳፬ (ሀያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች አዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው የንግድ ሚኒስቴር በአግባቡ እየተስተናገዱ እንዳልሆነ ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡
ጥቅምት 30 ቀን ድረስ መከፈል ያለበትን የዘንድሮ የግብር ግዴታ ለመወጣት ካዛንቺስ ወደ ሚገኘው የንግድ ሚኒስቴር ማምራታቸውን የጠቀሱት አንድ አስተያየት ሰጪ እዚያ ባዩት መስተንግዶ በጣም መደንገጣቸውን ተናግረዋል፡፡
በየዓመቱ የግብር መክፈያ መጠናቀቂያ ወቅት ሲቃረብ ሰዎች በብዛት መምጣታቸው የተለመደ ነው ያሉት ሌላ አስተያየት ሰጪ ሚኒስቴሩ አስቀድሞ ይህንን ሁኔታ በመገንዘብ በቀላሉ ማስተናገድ የሚችልበት አቅም መፍጠር ባለመቻሉ ያለው ሰልፍና ሁካታ እጅግ አሳዛኝ አድርጎታል ብለዋል፡፡
አንድ ሰው የግብር ግዴታውን ለመወጣት ወደ ግብር አስገቢው መ/ቤት ሄዶ የሚጉላላበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንዳልገባቸው የጠቀሱት የአንድ ኩባንያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሚኒስቴሩ ችግሩን ሳያስተካክል ግብር ለመሰብሰብ መቀመጡ ከፈረሱ ጋሪውን የማስቀደም ያህል ነው፡፡መጀመሪያ ግብር የመሰብሰብ አቅሙን ሊፈትሽ ይገባዋል ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
በክልል ከተሞች ህዝቡ ከገቢው ጋር ያልተጣጣመ ግብር እንዲከፍል መገደዱን መዘገባችን ይታወሳል።